Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ሰርተፊኬት የሌላቸው የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን ከስራ የሚያግድ አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው

BS Bethelhem Solomon Jun 24, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 132 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ሰርተፊኬት የሌላቸው የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችን ከስራ የሚያግድ አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው

የሰርቲፊኬሽን ስርዓቱን በአገር አቀፍ ደረጃ አስገዳጅ የማድረግ ሂደቱ ዓመታትን ሊፈጅ የሚችል ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ዝግጅቱና የተግባር እንቅስቃሴው በይፋ መጀመሩ ተመላክቷል።

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን ብቃት ለማረጋገጥና የዘርፉን ጥራት ለመጠበቅ የሚያስችል አዲስ አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

አዲሱ አሰራር በዘርፉ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ የሙያ ደረጃ ድረስ በአግባቡ ሰልጥነውና ህጋዊ የብቃት ማረጋገጫ (ሰርቲፊኬሽን) ስርዓት ውስጥ አልፈው ወደ ስራ እንዲሰማሩ የሚያስገድድ ነው።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (/) እንደገለጹት በዘርፉ የሚስተዋሉ የጥራት ችግሮችን ለመፍታትና የባለሙያዎችን ብቃት ለማረጋገጥ ስልጠና፣ ምዘና እና ሰርቲፊኬሽን በአንድ ላይ የተሳሰረ ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ ነው።|

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ለዚህም ስራ ስኬታማነት ሚኒስቴሩ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን  የሁለቱ ተቋማት የጋራ ጥረት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ማዕከላትን በመጠቀም የሰርቲፊኬሽን ስርዓቱን ተደራሽ እና ውጤታማ ለማድረግ ያለመ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም አሰራሩ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው ወደፊት ሰርተፊኬት የሌላቸው ባለሙያዎች በየትኛውም ደረጃ በሚገኙ የኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ እንዳይሳተፉ የሚያግድና ሙሉ በሙሉ አስገዳጅ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

ይሁን እንጂ ህጉን ሙሉ በሙሉ አስገዳጅ አድርጎ ወደ ተግባር ከመገባቱ በፊት ለባለሙያዎች ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የቅድመ ሁኔታ ስራዎችን የማጠናቀቅ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።


ይህ እርምጃ የተወሰደው በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እየታየ ያለውን አሳሳቢ የጥራት መጓደል ለመቅረፍ ሲሆን በዋናነት የጥራት መጓደል እና ደረጃ በደረጃ የሚተገበር የመመዘኛ ስርዓት አለመኖር በችግርነት ይጠቀሳሉ።


በተጨማሪም የባለሙያ ብቃት ማረጋገጫ ስርዓት አለመኖር የዘርፉን ስም እና ጥራት የጎዳ ሲሆን  አንድ ባለሙያ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ወደ ስራ ከገባ በኋላ በስራ ሂደት ውስጥ የሙያ ብቃቱን የሚለካ ወይም የሚያድስ ስርዓት አለመኖሩም ተጠቃሽ ነው።


በዚህም ምክንያት ብቃት የሌላቸው ሰዎች ሳይመዘኑ "መሐንዲስ" በሚል መጠሪያ ስራ ላይ መሰማራታቸው ለግንባታ ጥራት መጓደል እንደ ዋና ምክንያት ይነሳል።


በሌላ በኩል ልምድ ያላቸውና የበቁ ባለሙያዎች ለተሻለ እድል ወደ ውጭ አገራት  እየተሰደዱ መሆናቸው በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ክፍተት የፈጠረ ሲሆን በሀገር ውስጥ የሚቀሩት ባለሙያዎች ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር የሚተዋወቁበት ተቋማዊ አሰራር ስለሌለ በዘርፉ አቅም እየገነቡ ከመሄድ ይልቅ እያጠፉ በመማር ሂደት ውስጥ እንዲቆዩ ተገደዋል።


አሁኑ አሰራር አንድ ኮንትራክተር ውል ገብቶ ስራ ከጀመረ በኋላ ግንባታውን በጥራትና በተቀመጠለት ጊዜ መፈፀሙን መቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ ስርዓት ባለመኖሩ የጥራት መጓደል አደጋ ተጋርጦበታል


ይሁን እንጂ
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባለሙያዎች የሚሰለጥኑበት፣ የሚመዘኑበት እና ለሙያ ስነ-ምግባር ጉድለት የሚቀጡበትን አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ስርዓት እየዘረጋ ይገኛል።


የሰርቲፊኬሽን ስርዓቱን በአገር አቀፍ ደረጃ አስገዳጅ የማድረግ ሂደቱ ዓመታትን ሊፈጅ የሚችል ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ዝግጅቱና የተግባር እንቅስቃሴው በይፋ መጀመሩ ተመላክቷል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

19 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።