በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰጠውን የሁለተኛ ዲግሪ (የማስተርስ) መርሃ ግብር ወደ አራት ዓመት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አስታወቋል።
ባለስልጣኑ ይህንን ያስታወቀው አሁን ላይ ያለው የመማር ማስተማር ሂደት ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች እና በቅርቡ ከጸደቀው የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ጋር አለመጣጣሙን በመጥቀስ ነው።
ባለስልጣኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የ11 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው አሁን ያለው አሰራር ካልተቀየረ በስተቀር ወደፊት ለሚመረቁ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃ እውቅና ለመስጠት ትልቅ ተግዳሮት ይፈጥራል።
በዚህም ችግሩ በተለይም በውጭ ሀገራት ተምረው ለሚመለሱ እና የብቃት ማረጋገጫ ለሚጠይቁ ተማሪዎች ሰነድ ምዘና ሂደት ላይ ትልቅ አነጋጋሪ አጀንዳ መሆኑ ተገልጿል።
በ2017 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው “የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ደንብ” ከውጭ ተቋማት የተገኙ የብቃት ማረጋገጫዎችን ከሀገሪቱ መስፈርት ጋር አዛምዶ ለመስጠት ቢደነግግም አሁን ባለው የትምህርት አወቃቀር ይህንን መተግበር አዳጋች ሆኗል።
በተለይም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ሳያመጡ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ከተማሩ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የሚጠይቁት የብቃት ማረጋገጫ በባለስልጣኑ ዘንድ ከፍተኛ ክርክር እየፈጠረ ይገኛል።
የችግሩ መነሻ እንደሆነ የተጠቆመው የአማራጭ የትምህርት ክሬዲት ስርዓት አጠቃቀም ሲሆን ባለስልጣኑ እንደገለጸው በአውሮፓ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ተግባራዊ የሚደረገው የECTS መስፈርት በኢትዮጵያ ደንብ ውስጥ ከተቀመጠው አቀራረብ ጋር ሲነጻጸር ጉድለት አለበት።
ይህንን የክሬዲት ሰዓት ወደ ትምህርት ዓመታት ሲለወጥ የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሙ ቢያንስ የአራት ዓመት ቆይታ ሊኖረው እንደሚገባ የሚያስገድድ ሲሆን አሁን ያለው የሁለት ዓመት መርሃ ግብር በኢትዮጵያ በወጣው አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ደንብ መሰረት ሲመዘን መስፈርቱን የሚያሟላ ሆኖ አለመገኘቱ የባለስልጣኑን ስጋት አባብሶታል።
ይህንን የትምህርት ጥራት ማሻሻያ እና የብቃት ማረጋገጫ መደራረብ ለመቅረፍ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጉዳዩን ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም ለትምህርት ሚኒስቴር በደብዳቤ ማሳወቁን የገለጸ ሲሆን ነገር ግን እስካሁን ድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢው ምላሽም ሆነ መፍትሄ አለመገኘቱ በሪፖርቱ ተነስቷል።
የባለስልጣኑ አመራሮች እንደገለጹት ይህ የማሻሻያ ጥያቄ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና የምሩቃንን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለመጠበቅ የሚከናወን እንጂ ለተማሪዎች ተጨማሪ ጫና ለመፍጠር የታለመ አይደለም።
ይሁን እንጂ ጉዳዩ በአስቸኳይ ካልተፈታ የምሩቃን የትምህርት ማስረጃ ተቀባይነት በማጣት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሥራ ገበያ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ጉዳዩን እንዴት እንደሚፈቱት እና የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሙን አወቃቀር ወደ አራት ዓመት ለማሳደግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ መታየት ያለበት ጉዳይ ሆኗል።