በኢትዮጵያ የሚገኙ እና እድሜያቸው ለጡረታ የደረሰ ነገር ግን በጡረታ ሥርዓቱ ውስጥ ያልተካተቱ ዜጎች ሁሉ የመንግስት የጡረታ አበል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር ጥሪ አቅርቧል።
ማህበሩ ይህንን ጥያቄ ያነሳው አሁን ባለው የጡረታ አሠራር ውስጥ ተቀጥረው የማይሰሩ በኢ-መደበኛ ዘርፍ የነበሩ ወይም በሌሎች ዘርፎች ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ አረጋውያን የጡረታ መብት ተጠቃሚ አለመሆናቸው ኢ-ፍትሃዊ ስለሆነ መሆኑን አስረድቷል።
ማህበሩ የዚህን አዲስ የጡረታ አበል ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል መፍትሄም ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም መሰረት ይህንን የጡረታ ፈንድ ለማጠናከር የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች እንዲሰበሰብ ሀሳብ አቅርቧል።
በዚህ አግባብ የሚገኘው ገቢ የጡረታ ሽፋን ለሌላቸው አረጋውያን የገቢ ምንጭ እንዲሆንና የኑሮ ጫናቸውን እንዲቀንስ ያለመ መሆኑንም ገልጿል።
የማህበሩ ምክትል የቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ ጥያቄውን በተመለከተ ዝርዝር አተገባበር የያዘ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደርና ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መገባቱን ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው እንዳስረዱት በየትኛውም የስራ መስክ የተሰማራ ዜጋ ሀገሩን በማገልገሉ ሊከበርለትና በዕድሜ ማምሻው ሊጦር ይገባል።
ይህንን ሀሳብ እንዲያነሱ ያነሳሳቸው ዋናው ምክንያት ደግሞ በኢትዮጵያ እየተዳከመ የመጣው ባህላዊ የቤተሰብ ድጋፍ ሥርዓት መሆኑን ገልጸው አረጋውያን እንደ ቀድሞው በቤተሰብ የተከበቡ አይደሉም ብለዋል።
በኑሮ ውድነትና በኑሮ ውጣ ውረድ ምክንያት ልጆች ለወላጆቻቸው ድጋፍ ማድረግ እየተሳናቸው ወደ ራሳቸው ኑሮ በመገፋታቸው አረጋውያን በባዶ ቤት ያለ ጧሪ እየቀሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የማህበሩ ጥያቄ በአገሪቱ እየተቀየረ የመጣውን ማህበራዊ መስተጋብርና አረጋውያን በኢኮኖሚው ላይ እየደረሰባቸው ያለውን ተፅዕኖ መሰረት ያደረገ ሲሆን መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት አይቶ በጉዳዩ ላይ ምን ዓይነት ምላሽና ውሳኔ እንደሚሰጥ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሆኗል።
በሌላ በኩል ከሰሞኑ ማህበሩ የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የገነባቸውን ህንፃዎች ገቢ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ የአስተዳደሩን የገቢ ማግኛ ጥረቶች እንደ አንድ የማካካሻ መንገድ መመልከቱ ይታወሳል።
የመንግስት ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በአዲስ አበባ 4 ህንፃዎች፣ በባህር ዳር፣ በጅማ፣ በሐረር እና በሐዋሳ (እያንዳንዳቸው 1 ህንፃ) በድምሩ ስምንት ህንፃዎችን ገንብቷል።
የማህበሩ ምክትል የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ እንዳስታወቁት ከእነዚህ ህንፃዎች የሚገኘው ገቢ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለጡረታ ለወጡ አረጋውያን እንዲውል ተወስኗል።
አብዛኛዎቹ ጡረተኞች የሚያገኙት አበል ለኑሮ እጅግ አነስተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው ምንም እንኳን መንግስት በ2011 ዓ.ም 69 በመቶ እና በ2015 ዓ.ም ደግሞ 76 በመቶ የጡረታ አበል ጭማሪ ቢያደርግም አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር የሚደረገው ድጋፍ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ያነሳሉ።