ቻይና የአካባቢውን አቅርቦት ለማጠናከር 400 የትከሻ ፀረ-አውሮፕላን ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ለኢራን ልትልክ መሆኑን የውጭ መገናኛ ብዙኃን በሰፊው ዘግበዋል።
የቤጂንግ መንግሥት ውንጀላውን ሙሉ በሙሉ “መሰረተ ቢስ” በማለት በጥብቅ ቢክደውም ይህ የ70 ሚሊዮን ዶላር ሚስጥራዊ ስምምነት በቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ እና በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል ያለውን ግንኙነት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ እንደሚከተው ተመላክቷል።
በሆንግ ኮንግ በሚገኘው “ዞንግቺንግ ባኦሻንግ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት” የተባለ አማካሪ ድርጅት በኩል የተፈረመው ይህ ውል የQW-12 እና የFN-16 ዓይነት የትከሻ ፀረ-አውሮፕላን ሚሳይሎችን ያካተተ ነው ተብሏል።
እነዚህ በነጠላ ግለሰብ ሊሸከሙ የሚችሉ ኃይለኛ መሳሪያዎች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ይህ ግዢ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ከተጀመረው ጦርነት ወዲህ የአጭር ርቀት የአየር መከላከያ አቅሟን እና የጦር መሳሪያ ኪሳራዋን ለመተካት ካደረቻቸው ትላልቅ እና ታሪካዊ ጥረቶች አንዱ እንደሆነ ተነግሯል።
የአሜሪካ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ቻይና ከዚህ ቀደም ለባለስቲክ ሚሳይሎች ማገዶ የሚሆኑ ኬሚካሎች እና ለድሮን ማምረቻ የሚሆኑ ወሳኝ ቁሳቁሶችን ለቴህራን ልካለች።
ቻይና ለኢራን ከምታደርገው የጦር መሳሪያ ድጋፍ በተጨማሪ የኢራንን ነዳጅ በቀን ከ1.5 ሚሊዮን በርሜል በላይ በመግዛት ለሀገሪቱ ከፍተኛ የገንዘብ ገቢ እያስገኘችላት የሚገኝለት ሲሆን ይህም ኢራን ጦርነቱን እንድታስቀጥል የገንዘብ አቅም እየሰጠቻት መሆኑን ያሳያል።
የነዳጅ ገበያ ተንታኞች እንደገለጹት ቻይና በመጋቢት ወር ብቻ ከኢራን የምትገዛው የዕለት ተዕለት የውጭ ነዳጅ መጠን 1.6 ሚሊዮን በርሜል ደርሷል። ይህ አኃዝ እ.ኤ.አ. በ2025 ዓመታዊ አማካይ ከነበረው የቀን 1.4 ሚሊዮን በርሜል ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
ምንም እንኳ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና አቻቸው ጋር ባደረጉት የዲፕሎማሲያዊ ጉብኝትና ውይይት ዢ ጂንፒንግ ለኢራን የጦር መሳሪያ ላለመላክ ጥብቅ ቃል መግባታቸውን “ይህ ትልቅ መግለጫ ነው” በማለት ገልጸው የነበረ ቢሆንም አሁን የተደረሰው ሚስጥራዊ ስምምነት ግን የሁለቱን ሀገሮች መሪዎች ግንኙነት ወደ ከፉ ቀውስ ሊመራው ይችላል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሰፊው ግጭት እየተባባሰ በሄደበት በዚህ ወቅት ሳውዲ አረቢያ ከአሜሪካ ጋር በመሆን በኢራን ላይ ኃይለኛ ጥቃት የፈጸመች ሲሆን በሌላ በኩል ዩክሬን በካስፒያን ባህር ውስጥ የሚገኝ የኢራን የጭነት መርከብ ላይ ዒላማ አድርጋ መመታቷ ይታወሳል።
ይህ ድርጊት በኢራን እና በዩክሬን ጦርነቶች መካከል የመጀመሪያው ቀጥተኛ መተሳሰር መሆኑን የገለጹት የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንድሪ ሲቢሃ የኢራን የበቀል ዛቻዎች ምንም ዓይነት መሰረት የሌላቸው መሆናቸውን አፅንዖት ሰጥተዋል።