በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ የ2027-2028 የ“ሁበርት ኤች. ሃምፍሬይ” የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም ማመልከቻ ክፍት መደረጉን በይፋ አስታውቋል።
ይህ ፕሮግራም በመንግሥታዊ እና በግል ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ ያሉ በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች በአሜሪካ ቆይታቸው ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ እና ከአቻዎቻቸው ጋር ጠንካራ የሥራ ትስስር እንዲፈጥሩ የሚያስችል ልዩ ዕድል ነው።
በአሜሪካ መንግሥት ሙሉ ወጪ የሚሸፈነው ይህ ፕሮግራም የዲግሪ ትምህርት ሳይሆን የባለሙያዎችን የሥራ ብቃት ለመገንባት የተዘጋጀ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮግራሙ በተለይ በስድስት ዋና ዋና የሙያ ዘርፎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን እነዚህም ኮሙኒኬሽን እና ጋዜጠኝነት፣ ሕግ እና መልካም አስተዳደር፣ የተፈጥሮ ሀብት ፖሊሲ፣ የሕዝብ እና ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ የሕዝብ ጤና ፖሊሲና አስተዳደር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ፖሊሲና አስተዳደር ናቸው።
ለዚህ ፕሮግራም ብቁ ለመሆን አመልካቾች በርካታ መስፈርቶችን ማሟላት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል ዕድሜያቸው ከ32 እስከ 45 ዓመት መሆን፣ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ መያዝ እና ከመጀመሪያ ዲግሪ በኋላ ቢያንስ የ5 ዓመት የሙሉ ጊዜ ፕሮፌሽናል የሥራ ልምድ ማሟላት ይገኙበታል።
አመልካቾች በአመራር ወይም በፖሊሲ ነክ ኃላፊነት ላይ ያሉ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የላቀ ችሎታ ያላቸው እና ፕሮግራሙን አጠናቀው ወደ ሀገር ሲመለሱ ያገኙትን ዕውቀት ለማህበረሰቡ ለማዋል ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ለማገልገል ቁርጠኛ የሆኑ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
በተጨማሪም ከተመረጡ በኋላ ለTOEFL ፈተና ለመቀመጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜጋ የሆኑ ወይም በሀገሪቱ የተሰጠ ሕጋዊ ፓስፖርት ያላቸው ቋሚ ነዋሪዎች መሆብናቸውም ዋነኛ መስፈርት ነው።
ኤምባሲው ለፕሮግራሙ ብቁ ያልሆኑትንም ለይቶ ያስቀመጠ ሲሆን በአሜሪካ ሀገር ውስጥ በሚገኝ ድኅረ-ምረቃ ለአንድ የትምህርት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የተማሩ ባለሙያዎች ለዚህ ፕሮግራም ማመልከት አይችሉም ተብሏል።
በተመሳሳይ መልኩ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ መንግሥት በሚደገፉ ማናቸውም ፕሮግራሞች ላይ የተሳተፉ አመልካቾችም ዕድሉ ተጠቃሚ መሆን አይችሉም።
ማመልከቻው ሙሉ በሙሉ በኦንላይን የሚከናወን ሲሆን አመልካቾች በድረ-ገጽ በኩል የሥራ ልምድ ዝርዝር፣የፕሮግራም ዕቅድ፣ ለቀረቡ ጥያቄዎች የተሟላ የጽሑፍ መልስ፣ ከሥራ ቦታ የሚገኝ የድጋፍ ደብዳቤ እና የትምህርት ማስረጃዎችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
ለዚህ የምዝገባ ሂደት የተቀመጠው የመጨረሻ ቀን ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም መሆኑን ኤምባሲው አስታውቆ ማመልከቻ ይዘው በአካል ኤምባሲው መገኘት እንደማያስፈልግ አጽንኦት ሰጥቷል።
በተጨማሪም የዚህ ፕሮግራም ተሳታፊዎች በቆይታቸው ወቅት ማንኛውም የቤተሰብ አባል አብሮ እንዲሄድ አይፈቀድም የተባለ ሲሆን ለተጨማሪ መረጃዎች የኤምባሲውን ድረ-ገጽ መጎብኘት ወይም የአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲን ማነጋገር እንደሚቻል ተጠቁሟል።