በኢትዮጵያ በርካታ ደንበኞችን ያፈሩ ዓለም አቀፍ የክሪፕቶ መገበያያ ተቋማት በኢትዮጵያን ብር የሚደረጉ የክሪፕቶ ምንዛሬ ግብይቶችን በይፋ እያቆሙ መሆኑ ተሰምቷል።
እንደ ባይናንስ (Binance)፣ ባይቢት (Bybit) እና የቴሌግራም ዋሌት (Telegram Wallet) ያሉ ታላላቅ የዓለም አቀፍ የክሪፕቶ መገበያያ መድረኮች የኢትዮጵያን ብር ከክሪፕቶ ግብይት ዝርዝር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ማውጣታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ እርምጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በክሪፕቶ ከረንሲ ግብይት አማካኝነት ሊፈጸሙ የሚችሉ የገንዘብ ማሸሽ፣ ለወንጀል ቡድኖች ድጋፍ መስጠት እና ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት እየወሰደ ካለው ጠንካራ የቁጥጥር እርምጃ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።
ምንም እንኳን የክሪፕቶ መገበያያ መድረኮች በማዕከላዊ ባንኮች ቁጥጥር ስር የማይውሉ እና መገኛቸውንም ለመለየት አዳጋች ቢሆኑም ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን እና እንደ ቴሌብር ያሉ የሀገር ውስጥ የገንዘብ ማስተላለፊያ ተቋማትን የቁጥጥር አካል በማድረግ እንዲሁም ለተቋማቱ ባስተላለፈው ጥብቅ መመሪያ ግብይቱን ለማስተካከል ተንቀሳቅሷል።
በርካታ ወጣቶች ክሪፕቶ ከረንሲን እንደ ውጭ ምንዛሬ ንግድ (Forex Trading)፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ዲጂታል ክፍያ ለመፈጸም እና በውጭ ለሚገኙ ድርጅቶች በሰሩት የርቀት ሥራ ክፍያ ለመቀበል ይጠቀሙበት ነበር።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብር ከክሪፕቶ ግብይት መድረኮች መወገዱ ክፍያቸውን በክሪፕቶ መቀበል ቢችሉም ወደ ብር መንዝረው መጠቀም አለመቻላቸው የሥራ እንቅስቃሴያቸውን በእጅጉ አቀዛቅዞታል።
በተለይም በፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም እና ሊንከድን ላይ የማስታወቂያ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ክፍያ ለመፈጸም የገጠማቸው ችግር ሥራቸውን ለማቋረጥ እስከመገደድ አድርሷቸዋል።
ምንም እንኳን ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ ግብይቱን በይፋ ለማስቆም ያለመ ቢሆንም በዘርፉ ያሉ አካላት ግን በሌላ አማራጭ ለመቀጠል እየሞከሩ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አዲሱ የክሪፕቶ ግብይት በኢትዮጵያ ብር እየተካሄደ ያለው ገዥ እና ሻጮችን በኮሚሽን ክፍያ በሚያገናኙ ሦስተኛ ወገን ደላሎች አማካኝነት ነው።
እነዚህ አካላት የክሪፕቶ መድረኮች ከገበያ ያስወጡትን የኢትዮጵያ ብር ዝውውር ከዓለም አቀፉ ዲጂታል ገበያ ሙሉ በሙሉ እንዳይከስም እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህ የሚያሳየው የመንግሥት ጥረት ቢኖርም በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት አዳዲስ እና ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ የግብይት መንገዶችን እየፈጠረ መምጣቱን ነው።
ባንኩ የቴክኖሎጂ እገዳ በማድረግ መድረኮቹን ለመዝጋት ጥረት ቢያደርግም አብዛኛው ተጠቃሚ የቪፒኤን ቴክኖሎጂን በመጠቀም እገዳውን በማለፍ ግብይቱን ለመቀጠል መሞከሩ የቁጥጥር ስራው ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ያሳያል።
በቀጣይም በዘርፉ የሚኖረው የቁጥጥር ጥብቅነት እና የወጣቶች የሥራ አማራጮች አሳሳቢ ሆኖ እንደሚቀጥል ተገምቷል።