Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ቢዝነስ

ባለሥልጣኑ በነዳጅ መቅጃ ማሽኖች ላይ ቅሸባ ሲፈጽሙ የነበሩ ማደያዎችን አገደ

BS Bethelhem Solomon Jul 9, 2026 Updated 4h ago 2 ደቂቃ ንባብ 726 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ባለሥልጣኑ በነዳጅ መቅጃ ማሽኖች ላይ ቅሸባ ሲፈጽሙ የነበሩ ማደያዎችን አገደ

አንድ ሊትር ነዳጅ ሲቀዳ ሙሉ ሊትር መሆን ሲገባው፤ በአንዳንድ ማደያዎች በሚደረግ ሕገ-ወጥ ቅሸባ መጠኑ ወደ 800 ወይም 900 ሚሊ ሊትር እየወረደ እንደሚገኝ ተገልጿል።


የነዳጅና
ኢነርጂ ባለሥልጣን በነዳጅ ማደያዎች ላይ እያካሄደ ባለው አጠቃላይ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ በተጠቃሚዎች ላይ የነዳጅ ቅሸባ ሲፈጽሙ የተገኙ ማደያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል።

ባለሥልጣኑ ከግንቦት 29 ቀን 2018 . ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ባካሄደው ድንገተኛ የኢንስፔክሽን ስምሪት 12 የነዳጅ ማደያዎች የመቅጃ ማሽኖቻቸው (ዲስፔንሰሮች) ትክክለኛውን የልኬት መጠን እንደማያሳዩና ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙባቸው እንደነበር አረጋግጧል።

በዚህም መሠረት ባለሥልጣን /ቤቱ እንደ ጥፋታቸው መጠን ከሐምሌ 2 ቀን 2018 . ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን በዛሬው እለት አስታውቋል።


በዝርዝሩ መሠረት 3 ማደያዎች የሁለት ወር፣ 1 ማደያ የአንድ ወር የነዳጅ ጭነት ዕገዳ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ለቀሪዎቹ 6 ማደያዎች ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።


የባለሥልጣኑ
መግለጫ እንደሚያሳየው እርምጃው በዋናነት የሚያተኩረው ማደያዎች የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን መተግበር እና የመቅጃ ማሽኖቻቸው በወቅቱ ካሊብሬት (ልክ መስተካከል) መደረጋቸውን በማረጋገጥ ላይ ነው።


Advertisement
Your ad could be here — contact us

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር / ደስታው መኳንንት ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የተወሰደው እርምጃ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ማህበረሰቡን ከሚደርስበት ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት ለመጠበቅ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።


ዋና ዳይሬክተሩ አንድ ሊትር ነዳጅ ሲቀዳ ሙሉ ሊትር መሆን ሲገባው፤ በአንዳንድ ማደያዎች በሚደረግ ሕገ-ወጥ ቅሸባ መጠኑ ወደ 800 ወይም 900 ሚሊ ሊትር እየወረደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


ለትነት የሚፈቀድ አነስተኛ ልዩነት መኖሩንም ገልጸው ከዚያ በላይ የሚደረግ ቅሸባ ግን በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሕገ-ወጥነት ነው በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።


አሽከርካሪዎች እና የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች እርምጃው በነዳጅ አቅርቦት ላይ መስተጓጎል እና መጉላላት ይፈጥራል የሚል ስጋት ማቅረባቸውን ተከትሎ ዋና ዳይሬክተሩ ገበያውን ለማረጋጋት በሚል ሰበብ ህገ-ወጦችን መሸፈን ተገቢ አይደለም ብለዋል።


አያይዘውም በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ከሦስት እስከ አምስት በላይ ማደያዎች ያሉ በመሆኑ በተወሰኑ ማደያዎች ላይ የተወሰደው የእገዳ እርምጃ በአጠቃላይ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚፈጥረው ችግር የለም ብለዋል።


በተጨማሪም እስካሁን በተወሰዱ እርምጃዎችም ምንም ዓይነት 'ክሪቲካል' የሆነ የአቅርቦት እጥረት አለመፈጠሩን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ባለሥልጣኑ የማደያዎቹን የመቅጃ ማሽኖች የካሊብሬሽን ሁኔታ፣ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት አፈጻծምና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን የመቆጣጠር ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።


ባለሥልጣኑ ለነዳጅ ማደያዎች የነዳጅ አቅርቦት ትስስር ፈቃድ ሲሰጥ ህብረተሰቡን በታማኝነትና በፍትሃዊነት እንዲያገለግሉ መሆኑን በማስታወስ፤  የፈቃድ ግዴታቸውን ቸል ብለው በተሳሳተ ልኬት ተገልጋዩን የሚጎዱ ማደያዎች ላይ ጠንከር ያለ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚቀጥል አስጠንቅቋል።


በመጨረሻም የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ህብረተሰቡ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚፈጸሙ ማናቸውንም ዓይነት ጥፋቶች ወይም የልኬት ቅሸባዎች ሲያጋጥሙት ለባለሥልጣን /ቤቱ በመጠቆም ለቁጥጥር ሥራው የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

53 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።