የሱዳን መደበኛ የጦር ኃይሎች በሀገሪቱ ደቡብ ምስራቅ ሰማያዊ አባይ (ብሉ ናይል) ግዛት ውስጥ የምትገኘውን እና ከኢትዮጵያ ጋር በምትካለለው ድንበር ላይ የምትገኘውን ቁልፍ እና ስትራቴጂካዊ የኩርሙክ ከተማን መልሶ መቆጣጠሩን ሱዳን ትሪቡን አስነብቧል።
ከተማዋ ለወራት ያህል የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) እና የሱዳን ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ-ሰሜን (SPLM-N) አብደል አዚዝ አል-ሂሉ ቡድን ጥምረት በሆነው ታጣቂ ኃይል ስር ቆይታለች።
የሱዳን ጦር አራተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር እና ልዩ ግብረ ኃይሎች በከተማዋ ዳርቻዎች ላይ ለአምስት ቀናት ያህል ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ሲያካሂዱ ከቆዩ በኋላ ነው ረቡዕ ዕለት ወደ ከተማዋ መግባት የቻሉት።
በጦሩ የቪዲዮ መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው በዘመቻው ወቅት በታጣቂ ቡድኖቹ ላይ ከፍተኛ የሰው ኃይል እና የወታደራዊ ንብረት ውድመት የደረሰ ሲሆን ታጣቂዎቹም አካባቢውን ጥለው ወደ ደቡብ አቅጣጫ መሸሻቸውን የጸጥታ ምንጮች ገልጸዋል።
ኩርሙክ ከኢትዮጵያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በቀጥታ የምትዋሰን በመሆኗ በሱዳን፣ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን የየብስ ትራንስፖርት እና የወታደራዊ አቅርቦት መስመር ለመቆጣጠር እጅግ ወሳኝ ስፍራ ነች።
ታዲያ አማጺያኑ ባለፈው መጋቢት ወር ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ፤ በድንበር አካባቢው ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እና የነዋሪዎች መፈናቀል አስከትሎ ነበር ይታወሳል።
የኩርሙክ ከተማ ከእጅ መውጣት የRSF ታጣቂዎች ወደ መካከለኛው ሱዳን ለማድረግ ለነበረው ወታደራዊ ስምሪት ትልቅ ውድቀት መሆኑን የፖለቲካ እና የደህንነት ተንታኞች ይናገራሉ።
የከተማዋን ነጻ መውጣት ተከትሎ በሰማያዊ አባይ ግዛት ዋና ከተማ በዳማዚን ህዝባዊ ደስታ የተገለጸ ሲሆን የአካባቢው አስተዳደር በውጊያው ሳቢያ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም እና ተፈናቃዮችን ለመመለስ ኮሚቴ ማዋቀር መጀመሩን አስታውቋል።
የኩርሙክ ከተማ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ታሪክ ውስጥ በወታደራዊ ስልታዊ ጠቀሜታዋ የምትታወቅ ቦታ ስትሆን እስከ አሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ከፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) ወገን የተሰጠ ይፋዊ ምላሽ የለም።
ከ2023 ዓ.ም. ጀምሮ በሱዳን የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት እስካሁን ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደግሞ ለአስከፊ ሰብአዊ ቀውስ እና መፈናቀል ዳርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ቀርበው ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የሱዳንን ጉዳይ በማንሳት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቅንጣት ታክል ስጋት እንደሌላቸው መግለጻቸው ይታወሳል።