አንዳንድ የጤና ተቋማት ለጤና መድን ተጠቃሚ ታካሚዎች "መድሃኒት የለም" የሚል ምላሽ እየሰጡ በዚያው ሰዓት ግን በራሳቸው ሂሳብ ካሽ ለሚከፍሉ ታካሚዎች ያንኑ መድሃኒት በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በፓርላማ ባቀረበው የ11 ወራት ሪፖርት አጋለጠ።
ተቋሙ በዛሬው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ባቀረበው ሰፊ ሰነድ የጤና መድን አባላት እና ቤተሰቦቻቸው በውል ከተያያዙባቸው ተቋማት ያለ ክፍያ መድሃኒት የማግኘት መብት ቢኖራቸውም በተግባር ግን በከፍተኛ እንግልት ውስጥ መሆናቸውን አስረድቷል።
ይህ አድሎአዊ አሰራር ተገልጋዮችን ለተጨማሪ ወጪና አስተዳደራዊ በደል እየዳረገ እንደሚገኝም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በዚህም የጤና ተቋማት ለተጠቃሚዎች መድሃኒት እንደሌለ ቢገልጹም ክፍያ ለሚፈጽሙ ታካሚዎች ግን መድሃኒቶቹን ማቅረባቸው የጤና መድን ስርአቱን ዓላማ የሚቃረን እና የዜጎችን መብት የሚጥስ ድርጊት መሆኑን ተቋሙ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በተጨማሪም በጤና ተቋማት ውስጥ የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት ቢዘረጋም ግልጽ የሆነ የአሠራር ሂደት ባለመኖሩ ተገልጋዮች ቅሬታቸውን በቀላሉ ማቅረብ እንዳልቻሉ አክሏል።
መድሃኒት በአይነትና በመጠን እየቀረበ ባለመሆኑ የማህበረሰብ ጤና መድን ተጠቃሚዎች ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን የጠቀሰው እንባ ጠባቂው ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ እና የጤና ተቋማት ያለባቸውን የአሰራር ክፍተቶች እንዲያርሙ በጥብቅ አሳስቧል።
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በ14 ገጽ ባቀረበው በዚህ ሪፖርት ከጤናው ዘርፍ መዛባት በተጨማሪ ተቋሙ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ በሚለቀቅበት እና ለንብረት ካሳ በሚከፈልበት ሁኔታ ላይ "ስልታዊ" ያለውን ምርመራ ማካሄዱን ጠቅሷል።
በዚህም መሰረት ተነሺዎች ከመነሳታቸው በፊት ቢያንስ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ ስለ ልማቱ አይነትና ጠቀሜታ ግንዛቤ እንደማይሰጣቸው ንብረታቸው ሳይለካና ካሳ ሳይወሰን በሃይል እንደሚነሱ ካሳ ከተወሰነላቸው በኋላም ክፍያው ለዓመታት እንደሚዘገይ ተቋሙ በሪፖርቱ አጋልጧል።
ምንም እንኳን እንባ ጠባቂው ድርጊቱ የተፈጸመባቸውን ቦታዎችና ጊዜ በግልጽ ባይጠቅስም እነዚህ አሰራሮች ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን ካሳ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣውን አዋጅ በግልጽ የሚቃረኑ መሆናቸውን አስረድቷል።
ባለንብረቶቹም ከቤት ንብረታቸው በሃይል ከተነሱ በኋላ መብታቸውን ለማስከበር በተለያዩ ተቋማት አቤቱታ ለማቅረብ መገደዳቸው በሪፖርቱ ተካቷል።
ተቋሙ ባለፉት 11 ወራት ብቻ ከ44 ሺህ 900 በላይ ሰዎችን የሚወክሉ 1,715 አቤቱታዎችን ተቀብሎ እየመረመረ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን እነዚህ በጤናና በልማት ስም የሚፈጸሙ የአሰራር ክፍተቶች የዜጎችን መብት እየገፈፉ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን እርምት እንዲወስዱ በጥብቅ አሳስቧል።