የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አዲስ ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም መሰረት በቀጣይ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ወቅት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ 1.2 ሚሊዮን ቤቶች መገንባታቸውን አስታውሰው፤ይህ ውጤት ለቀጣዩ እቅድ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የታቀደው የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ በዋናነት በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲሁም በሌሎች የጋራ የአጋርነት መንገዶች እንደሚከናወን ጠቅላይ ሚንስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል።
በተጨማሪም ለዚህ እቅድ መሳካት የሚያግዝ አዲስ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በካቢኔ በኩል መጽደቁን ጠቅሰው፤ ይህም የቤት ልማቱን ለማፋጠን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የግንባታ ዘርፉን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም የኮንስትራክሽን ግብዓት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ወደ ምርት መግባታቸውንና አቅርቦቱን ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አያይዘውም ዘርፉን በባለሙያ ለመደገፍ የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንና በከተማና በገጠር የቤት ግንባታ እንቅስቃሴዎች በተግባር መጀመራቸውን አብራርተዋል።
ይህም ለግንባታው ስራ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል እና ግብዓት በሀገር ውስጥ ለማሟላት የሚያስችል ስትራቴጂያዊ እንቅስቃሴ መሆኑ ተገልጿል።
የቤት ፋይናንስ ተደራሽነትን በተመለከተ መንግሥት የሞርጌጅ ሥርዓትን በማጠናከር፣ ዜጎች በረጅም ጊዜ ክፍያ ከገቢያቸው ጋር በሚመጣጠን መንገድ የቤት ባለቤት የሚሆኑበት አሠራር መዘርጋቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ይህ አሰራር በተለይም በቀጥታ ቤት መግዛት ለማይችሉ ዜጎች የቤት ባለቤትነትን እውን ለማድረግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አንስተው በዚሁ ወቅት የቤት ግንባታው የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ከመሙላት ባሻገር፣ የግንባታ ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ለብዙ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።
በተያያዘም መንግሥት በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ዓመታት በግብርናና በተለያዩ ዘርፎች ለ5 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በውጭ አገር የስራ ስምሪት ብቻ ከ600 ሺህ በላይ ዜጎች ብቃታቸውን በማረጋገጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን በመግለጫቸው አካተው አቅርበው ይህ ሁሉ ጥረት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል መንግሥት የያዘውን ሁለገብ ዕቅድ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
ይህ ዕቅድ በዜጎች ዘንድ የቤት ባለቤትነትን በተለይም በከተሞች እየተባባሰ የመጣውን የኪራይና የመኖሪያ ቤት እጥረት ችግር ለመፍታት የሚኖረው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።