Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ሳዑዲ አረቢያ በህገ ወጥ መንገድ ዕፅ ለማዘዋወር የሞከሩ ሶስት ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር አዋለች

BS Bethelhem Solomon Jul 20, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 416 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ሳዑዲ አረቢያ በህገ ወጥ መንገድ ዕፅ ለማዘዋወር የሞከሩ ሶስት ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር አዋለች

ተጠርጣሪዎችና የተያዙት ዕፆች ለሚመለከተው ህጋዊ አካል የተላለፉ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ህጋዊ ሂደቶች ተጠናቀው መላካቸው ተገልጿል።


በሳዑዲ
አረቢያ የዓሲር ክልል ድንበር ጠባቂ ቡድን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ የነበረን ከፍተኛ መጠን ያለው የዕፅ ዝውውር ማክሸፉን አስታውቋል። እንደ ቡድኑ ገለጻ ዕፁን ሊያዘዋውሩ የነበሩት ሶስት ኢትዮጵያውያን ናቸው።


የሳዑዲ መንግስት 17 ኪሎ ግራም ሃሺሽ እና 7 ሺህ 500 የአምፌታሚን አደንዛዥ ዕፅን የድንበር ደህንነት ህግን በመጣስ ወደ ሀገሪቱ ለማስገባት ሙከራ ያደረጉ ሶስት ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር አውሏል።


ይህ አደንዛዥ ዕፅ የማዘዋወር ሙከራ የተደረገው በድንበር ጠባቂ የከር ተቆጣጣሪዎች ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎቹ የድንበር ደህንነት ሕግን ጥሰዋል ተብለዋል።


ሳዑዲ ጋዜጣ እንደዘገበው ተጠርጣሪዎችና የተያዙት ዕፆች ለሚመለከተው ህጋዊ አካል የተላለፉ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ህጋዊ ሂደቶች ተጠናቀው መላካቸው ተገልጿል።


የሳዑዲ አረቢያ የደህንነት ባለስልጣናት ሀገሪቱን እና ወጣቶችን ከአደንዛዥ ዕፅ አደጋ ለመጠበቅ መሰል የድንበር ላይ ቁጥጥሮችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


በተጨማሪም የሳዑዲ የድንበር ጠባቂ ኃይል ማንኛውንም ከጫት እና አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ጋር የተያያዙ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ለህግ አስከባሪ አካላት ማሳወቅ እንደሚገባ አሳስቧል።


አያይዞም ማንኛውም የሚቀርብ ጥቆማ ሙሉ በሙሉ በሚስጥር እንደሚጠበቅ እና ጥቆማ ሰጪዎች ላይም ምንም ዓይነት የሕግ ኃላፊነት እንደማይኖር አረጋግጧል።


ከዚህ ቀደም የሳዑዲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በሪያድ የዕፅ አዘዋዋሪዎች መረብ ላይ በተወሰደ እርምጃ የኢትዮጵያ ዜጋን ጨምሮ 22 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።


የሀገሪቱ ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኔ ወር በሪያድ ከተማ በዕፅ ዝውውር እና ማሻሻጥ ወንጀል ላይ የተሰማራ የወንጀል ቡድንን ማፍረሱን በማስታወቅ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የውጭ ዜጎች መካከል አንድ ኢትዮጵያዊ እንደሚገኝበት አስታውቋል።


በሌላ በኩል ሲኤንኤን በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ የሞት ፍርድ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ዓመት ብቻ ገዳይ ባልሆኑ የአደንዛዥ ዕፅ ወንጀሎች የተገደሉት ቁጥር 71 ሲደርስ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የውጭ ዜጎች ይወክላሉ ሲል በዘገባው አትቷል።


የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በሳዑዲ በሕግ ሒደት ላይ በሚገኙና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው 1 ሺህ 971 በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የምህረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ማስታወቁ አይዘነጋም።


ባለፈው ዓመት በሳዑዲ አረቢያ በአጠቃላይ 356 ሰዎች ሲገደሉ ከእነዚህ ውስጥ 240 የሚሆኑት በአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል የተፈረደባቸው ሲሆን አብዛኛዎቹ የውጭ ዜጎች ናቸው።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

52 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።