በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በዘመናዊ መልኩ የተደራጁ እና ስሜትን መሰረት ያደረጉ የኦንላይን ማጭበርበር ወንጀሎች ሀገሪቱን እያሳሰቡ መምጣታቸውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
በርካታ ዜጎች “ውጭ ሀገር ነው የምኖረው”፣ “የፍቅር ጓደኛ አጥብቄ እፈልጋለሁ” እንዲሁም “ለሞት የሚዳርግ ከባድ በሽታ ይዞኛል፤ ነገር ግን ያለኝን እጅግ ብዙ ሀብት የሚያስተዳድርልኝ እና የሚወርስልኝ ታማኝ ሰው መምረጥ እፈልጋለሁ” በሚሉ የውሸት ሰበቦች እየተታለሉ ከፍተኛ ገንዘብ እየተዘረፉ ይገኛሉ።
አጭበርባሪዎቹ ሕገወጥ ድርጊታቸውን ለመፈጸም እንደ ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ እና ቴሌግራም ያሉ ታዋቂ የማህበራዊ መገናኛ መድረኮችን በስፋት ይጠቀማሉ ተብሏል።
አታላዮቹ መጀመሪያ ላይ ሰዎችን በጓደኝነት ጥያቄ በመቅረብ፤ “ከሚታዩት እና ከሚገኙት ሰዎች ሁሉ አንተን/አንቺን ብቻ መርጫለሁ” በሚል ማራኪና አሳሳች ቋንቋ የዒላማቸውን ስሜት ይቆጣጠራሉ።
በዚህም ሳቢያ ብዙዎች እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘባቸውንና ንብረታቸውን ለቀማኞች አሳልፈው እየሰጡ መሆናቸውን የዐቃቤ ሕግ መረጃ ያረጋግጣል።
የማጭበርበሩ መረብ እጅግ የጠነከረ እና በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን የተጠቆመ ሲሆን የወንጀሉ አፈጻጸም ሂደትም አስገራሚ መሆኑም ተነግሯል።
የመጀመሪያው አታላይ ከፍቅር ግንኙነትና ከሀብት ውርሰና ቃል ኪዳን በኋላ ራሱን ከሰወረ በኋላ፤ ሌላኛዋ ወይም ሌላኛው ተባባሪ በሌላ ስልክ ቁጥር እና በልዩ ስም በመደወል ተጎጂውን ያነጋግራሉ።
በመቀጠልም “ውድ የሆነና ዶላር እንዲሁም ወርቅ የያዘ ትልቅ ዕቃ ከውጭ ሀገር ተልኮልህ/ልሻል ጉምሩክ ደርሷል፤ ነገር ግን ዕቃውን ለመረከብ የተወሰነ የጉምሩክ ክፍያ መክፈል ይጠበቅብሃል/ሻል” በሚሉ አሳማኝ ንግግሮች አጭበርባሪዎቹ የተጎጂውን እምነት ለማግኘት የላኪና የተቀባይ ስም ያለበት የታሸገ ትልቅ የዕቃ ፎቶ በቴሌግራም ወይም በዋትስአፕ ይልካሉ።
ተጎጂውም በስጦታው ተማርኮ እና ዕቃው በእርግጥም መጥቷል ብሎ በማመን በተደጋጋሚ ገንዘብ በመላክ እስከ 500 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ እንዲያጣ ይደረጋል።
የግንኙነት ሂደቱ አብዛኛውን ጊዜ በፌስቡክ ተጀምሮ ወደ ግል መልዕክት ማቀበያ መድረኮች እንደ ዋትስአፕ እና ቴሌግራም እንደሚሸጋገር የተጠቆመም ሲሆን ህብረተሰቡ መሰል ወንጀሎች ሰለባ እንዳይሆን ጥልቅ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
ማንኛውም ሰው ከማያውቀው እና በአካል ከማይተዋወቀው አካል እንዲህ ዓይነት የፍቅርና የስጦታ ጥያቄ ሲቀርብለት “ካለው ሰው ሁሉ እኔ ለምን ተመረጥኩ?” በማለት መጠራጠር ይገባዋል ተብሏል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ ከ100 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ መጠን ያላቸው ከ80 በላይ ዋና ዋና የክስ መዝገቦች በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አማካኝነት በንጹሐን ዜጎች ላይ በተፈጸሙ የማጭበርበር ወንጀሎች ዙሪያ መመስረታቸው ታውቋል።
በየክፍለ ከተማው እና በሌሎች የታችኛው የስልጣን እርከኖች ላይ የተመሰረቱትን ሌሎች ተመሳሳይ የክስ መዝገቦች ሲታከሉበት ደግሞ፤ ችግሩ የደረሰበትን አጠቃላይ አሳሳቢ መጠን እና የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍ ያለ መሆኑን እንደሚያሳይ ተመላክቷል።