በህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እና ታክሲዎች ውስጥ የሞባይል ስልክ ድምጽ ከፍ አድርጎ በተለይም የቲክቶክ ቪዲዮዎችን ያለ የጆሮ ማዳመጫ (ኤርፎን) መጠቀም ተሳፋሪዎችን እየረበሸ እና አዲስ የድምጽ ጫና ፈተና እየሆነ መምጣቱ ተጠቆመ።
ከባድ ሰልፍ እና የትራንስፖርት መጨናነቅ ተቋቁመው ወደ ስራቸው የሚጓዙ ተሳፋሪዎች፤ በጉዞ ላይ እያሉ ከጎናቸው ያሉ ተጓዦች የሞባይል ስልክ ድምጾችን ያለ ገደብ በመልቀቃቸው ከፍተኛ ሰላም ማጣታቸውን ተናግረዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ተሳፋሪዎች ማንኛውንም ድምጽ ለመስማት ሳይገደዱ በሰላም ለመጓዝ ቢፈልጉም በግዴታ የሌሎችን የሚዲያ ልቀት እና ሃይማኖታዊ ይዘቶች ጭምር እንዲሰሙ እንደሚደረጉ ታዛቢዎች ያስረዳሉ።
ተሳፋሪዎች እንደሚያስረዱት በየታክሲው እና በየአውቶብሱ ውስጥ ስልካቸውን ታችና ላይ እያደረጉ የተለያዩ ምስሎችን የሚመለከቱ እና ድምጾችን ከፍ አድርገው የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።
ችግሩ ቲክቶክ ማየታቸው ሳይሆን የሚመለከቱት ቪዲዮ ድምጽ ለሌላው ተጓዥ በሚረብሽ መልኩ ከፍ አድርገው ማሰማታቸው መሆኑንም አስረድተዋል።
ድምጽ እንዲቀነሱ ሲጠየቁም አብዛኞቹ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው “ምን አገባህ በኛ ስልክ?” የሚል ምላሽ እንደሚሰጡ እና በኤርፎን ለማዳመጥ ፍላጎት እንደሌላቸው ተመላክቷል።
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳግም በልሁ ወንድሙ ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም የግል መብት ቢሆንም የሌላውን ሰው ሰላም አለመንካት ግን ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል።
የተሳፋሪዎችን ደህንነት እና ሰላም ለማስጠበቅ የተለያዩ መመሪያዎች በየጊዜው እንደሚወጡ ጠቁመው አሽከርካሪዎችና ረዳቶች የውስጥ ዲሲፕሊንን የማስፈጸም ሃላፊነት እና መብት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ቢሮው በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ጥናቶችን የጀመረ ሲሆን ጥናቶች ሲጠናቀቁ ተጨባጭ እርምጃ የሚወሰድበት አሰራር ይፋ እንደሚደረጉ ተመላክቷል።
በሌላ በኩል ጉዳዩን ከህግ አሰራር አንጻር የሚመለከቱት ጠበቃ እና የህግ አማካሪ አቶ ገድፈው ባንቲ ይህ ድርጊት በሀገራችን ህገ መንግስት አንቀጽ 44 እና አንቀጽ 92 የተደነገገውን ድንጋጌ የሚጥስ መሆኑን ለሸገር ሬድዮ ተናግረዋል።
ማንኛውም አካል በንጹህ አካባቢ የመኖር እና ያለመረበሽ መብት እንዳለው የገለጹት የህግ አማካሪው በህዝብ ማመላለሻ ውስጥ የሚፈጠረው የድምጽ ጫና እንደ አንድ የህግ ጥሰት እና የድምጽ ብክለት ሊታይ የሚችልበት አግባብ እንዳለም አብራርተዋል።
የግል ስብዕና ግንባታ አሰልጣኝ እና የስነ ልቦና ባለሙያዎች በበኩላቸው አንድ ሰው ገንዘብ ከፍሎ በሚያገኘው የትራንስፖርት አገልግሎት ደህንነቱ ተጠብቆ እና በሌሎች ሳይረበሽ ከፈለገው ቦታ የመድረስ መብት እንዳለው አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ይህንን መብት ጥሶ የሌሎችን ሰላም አደፍርሶ እንደፈለጉ መሆን ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።