የትምህርት ሚኒስቴር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ደረጃዎች ለሚያስተምሩ መምህራን የሚሆን "የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን የደረጃ እድገት አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1148/2018" በሚል የተዘጋጀ አጠቃላይ አዲስ መመሪያ ይፋ አድርጓል።
አዲሱ መመሪያ መምህራን ወደ ቀጣይ የደረጃ እድገት እርከኖች ለመሸጋገር ማሟላት የሚገባቸውን አዳዲስና ሰፊ መስፈርቶች ያካተተ ነው።
ከወጡት አዳዲስ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ አንድ መምህር ለደረጃ እድገት ለመብቃት ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች ውስጥ ቢያንስ 75 በመቶ የሚሆኑት 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸው በገለልተኛ አካል መረጋገጥ አለበት የሚለው ነው።
ይህ አሠራር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ የተማሪዎችን ውጤታማነት ከፍ ለማድረግ እንዲሁም የመምህራንን ኃላፊነትና ተጠያቂነት ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በአጠቃላይ መመሪያው በማስተማር ሥራቸው የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡ መምህራንን በትክክል ለማበረታታት፣ የሥራ ተነሳሽነታቸውንና ሞራላቸውን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም አጠቃላይ የትምህርት ጥራትን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
በወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት የአጠቃላይ ትምህርት መምህራን የእድገት መሰላል በሰባት ደረጃዎች የተከፋፈሉ ሲሆን እነሱም ጀማሪ መምህር፣ መለስተኛ መምህር፣ መምህር፣ ከፍተኛ መምህር፣ ተባባሪ መሪ መምህር፣ መሪ መምህር እና ከፍተኛ መሪ መምህር የሚሉ እርከኖች ናቸው።
ለመመሪያው አፈጻጸም የተቀመጠው የቆይታ ጊዜም በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን፤ ከጀማሪ ወደ መለስተኛ መምህርነት ለመሸጋገር ሁለት ዓመት ሲፈጅ፣ በቀጣዮቹ ደረጃዎች ደግሞ በእያንዳንዱ እርከን የሦስት ዓመታት ቆይታ የሚጠይቅ ነው።
ይሁን እንጂ መመሪያው ጥብቅ የዕድል ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን፤ አንድ መምህር በተከታታይ ወይም በተለያየ ጊዜ በውድድር ሁለት ጊዜ እድገት ማግኘት ካልቻለ ለሦስተኛ ጊዜ የመወዳደር ዕድል እንደማይኖረው ተደንግጓል።
መምህራን ለደረጃ እድገት ውድድር ብቁ ለመሆን ማሟላት ከሚገባቸው የጋራ መስፈርቶች መካከል በመምህርነት ሙያ ዕውቅና ካለው ተቋም የተመረቁ መሆን፣ የሙያ ፈቃድ ምስክር ወረቀት መያዝ እንዲሁም ለጀማሪ መምህራን የመውጫ ምዘና ማለፍ በዋናነት ተቀምጠዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጀማሪ መምህራን ቢያንስ የ40 ሰዓታት፣ ከመለስተኛ መምህር ጀምሮ ያሉት ደግሞ የ60 ሰዓታት ሙያ ተኮር አጫጭር ሥልጠናዎችን መከታተልና የተከታታይ ሙያ ማሻሻያ ዕቅዳቸውን በአግባቡ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
ወደ ከፍተኛ የእድገት እርከኖች ለመሸጋገር የተቀመጡት መመዘኛዎች የማስተማር ብቃትን ብቻ ሳይሆን የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ተሳትፎንም ያካተቱ ናቸው።
ሆኖም አዲሱ መመሪያ ልዩና የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መምህራን የተፋጠነ የደረጃ እድገት የሚሰጥበትን አሠራርም አብሮ አካትቷል።