Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡለትን የሚኒስትሮች ሹመት አጸደቀ

BS Bethelhem Solomon Oct 8, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 64 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡለትን የሚኒስትሮች ሹመት አጸደቀ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔውን ሲያዋቅሩ የትምህርት ዝግጅት እና የአስፈጻሚነት ሃይል ያላቸውን ከትምህርት ዝግጅታቸው ጋር ለማጣጣም መሞከራቸውንም ገልጸዋል።


የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ መስከረም 28፤ 2019 በተካሄደው 7ኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ አመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ካቢኔያቸውን  አዋቅረዋል።


በዚህም በዕጩነት ቀርበው ሹመታቸው ከጸደቀው 23 ሚኒስትሮች ውስጥ ዘጠኙ ባሉበት እንዲቀጥሉ የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በድጋሚ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይገኝበታል። 


እንዲሁም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር ፣ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ አቶ አዲሱ አረጋ የግብርና ሚኒስትር፣ ሀና አርዐያ ስላሴ የፍትሕ ሚኒስትር፣ ዶ/ር ሐብታሙ ኢተፋ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ ዶ/ር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስትር፣ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ የገቢዎች ሚኒስትር፣ ሰላማዊት ካሳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ባሉበት እንዲቀጥሉ ሹመታቸው ጸድቋል። 


በሌሎች የሚኒስቴር መስርያ ቤቶች ሲያገለግሉ የቆዩ እና አዲስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ላይ የተሾሙ ሚኒስትሮችም ሹመት የጸደቀ ሲሆን የአሁኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባኤ እና የቀድሞው የገንዘብ ሚኒስትርን በመተካት የቀድሞው ፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።


እንዲሁም የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሙሐመድ እድሪስ ወይዘሮ አይሻ ሙሐመድን በመተካት የሀገር መከላከያ ሚኒስትር ሆነዋል።በሌላ በኩል የቀድሞው የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ተሹመዋል።


በአዲስ ከተተኩት ውስጥ ደግሞ በዶ/ር ካሳሁን ጎፌ ይመራ የነበረው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ለመምራት የቀድሞ የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ወይዘሮ ያስሚን ወሃብ ረቢ ተሾመዋል።


የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት ፍሬህይወት ታምሩ የኢኖቬሽን እና ቴኖሎጂ ሚኒስትር በመሆን ሹመታቸው ጸድቋል።በተጨማሪም የቀድሞው የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍስሐ ይታገሱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ ሹመታቸው ጸድቋል።


የምሕንድስና ባለሞያው ኢ/ር ሙሐመድ ዓብዱራህማን ከሰሞኑ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙትን እና የቀድሞው የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር የነበሩትን ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒን ተክተዋል።


የቀድሞው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ያገለገሉት አቶ በረከት ፍስሐ ጽዮን ለአዲሱ ለብሄራዊ ስትራቴጂ ሚኒስትር፣ አቶ ሳዳት ነሻ በአሁኑ የሎጂስቲክስ ሚኒስትር እንዲሁም ወይዘሮ አለምጸሃይ ጳውሎስ የማዕድን ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።


የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ያገለገሉት አቶ አወሉ አብዲ የስራና ክህሎት ሚኒስትር፣ አቶ ሙሳ አደም የሰላም ሚኒስትር፣ ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር ሹመታቸው እና ዶ/ር አክሊሉ ታደሰ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ጸድቋል።


ስለ ሹመት ሂደቱ ማብራርያ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትሩ ጾታ፣ ብሄር እና እምነትን ያማካለ ለማድረግ ሞክረናል ያሉ ሲሆን ከተሾሙት 22 ሚኒስትሮች ውስጥ ዘጠኙ ሴቶች ናቸው።



ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔውን ሲያዋቅሩ የትምህርት ዝግጅት እና የአስፈጻሚነት ሃይል ያላቸውን ከትምህርት ዝግጅታቸው ጋር ለማጣጣም መሞከራቸውንም ገልጸዋል።


በተጨማሪም የስራ ልምድ ሌላው ነጥብ ነው ያሉ ሲሆን ውጤት ያስመዘገቡ እና የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን እና ቀጣዩን አመታት ያሳያሉ ተብሎ በሚጠበቀው ብቃት መሰረት ለመለየት ተሞክሯል ብለዋል።


“ሥልጣን ኮፍያ ነው! ጭንቅላት አይደለም። በማንኛውም ሰዓት ፀሐይ ካልበረታ፣ አስፈላጊ ካልሆነ ሊነሳ ወይም በክብር ሊቀመጥ ይችላል። ስለዚህ አገልጋይ መሆን ይገባል፤ እጃችንም ልባችንም ንፁህ መሆን አለበት” ሲሉም አሳስበዋል።


BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

88 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።