Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

የመንግስት ሰራተኞች በስራ ላይ ለመቆየትና እድገት ለማግኘት አዲስ የብቃት ምዘና ሊወስዱ ነው

BS Bethelhem Solomon Nov 7, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 88 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የመንግስት ሰራተኞች በስራ ላይ ለመቆየትና እድገት ለማግኘት አዲስ የብቃት ምዘና ሊወስዱ ነው

በጸደቁት ረቂቅ መመሪያዎች መሰረት በሶስቱም የመመዘኛ ዘርፎች ከ90 እስከ 100 በመቶ የሚያመጡ ሰራተኞች የሁለት እርከን የደሞዝ ጭማሪ የሚያገኙ ሲሆን ከ75 እስከ 90 በመቶ ላመጡ ደግሞ የአንድ እርከን ጭማሪ ይደረግላቸዋል።


የኢትዮጵያ
ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት ሰራተኞችን በባህሪ፣ በክህሎት እና በአገልግሎት አሰጣጥ ለመመዘን የሚያስችሉ 18 አዳዲስ መመሪያዎችን አጽድቆ ወደ ስራ ሊያስገባ እንደሆነ አስታወቀ።


መመሪያዎቹ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2016ን ለማስፈጸም የተዘጋጁ ሲሆን ማንኛውም ሰራተኛ በያዘው መደብ ለመቆየት፣ የደረጃ እድገትና ዝውውር ለማግኘት፣ እንዲሁም የወደፊት የደመወዝ ጭማሪ ለማግኘት የቴክኒካል፣ የባህሪ እና የተግባር ብቃት ምዘናዎችን መወሰድ እንደሚገባው ተደንግጓል።

 

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የአስተዳደር ፍርድ ቤት ተጠሪ ዳኛ አቶ መስፍን ረጋሳ አንድ ሰራተኛ በስራ ላይ ለመቆየት በባህሪያዊ፣ በቴክኒካል እና በተግባር ምዘናዎች በሶስቱም መስፈርቶች እያንዳንዳቸው ቢያንስ 70 በመቶ ውጤት የማምጣት ግዴታ እንዳለበት ለሸገር ሬድዮ ገልጸዋል።


 ምዘናዎቹ የዘልማድ አስተያየቶችን ሳይሆን በሳይንስ የተረጋገጡ የቡድን ስራ፣ ተምሳሌትነት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ስነ-ምግባር ባህሪያትን መሰረት ያደረጉ ናቸው።


በምዘናው የሚያልፍ ሰራተኛ ለአምስት አመታት የሚያገለግል የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሚሰጠው ሲሆን 70 በመቶ ማምጣት ያልቻሉ ሰራተኞች ግን ወዲያውኑ ከመስሪያ ቤቱ እንደማይሰናበቱ ታውቋል።


እነዚህ
ሰራተኞች አስፈላጊው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በየስድስት ወሩ አዘጋጅቶ ዳግም ምዘና የመስጠት ግዴታ በመስሪያ ቤቱ ላይ ተጥሏል።



ሆኖም በምዘናው በቂ ውጤት ማምጣት ያልቻሉ እና መቀጠል የማይፈልጉ ሰራተኞች ጥቅማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በገዛ ፈቃዳቸው ከስራ መልቀቅ የሚችሉበት ህጋዊ አሰራር በረቂቅ መመሪያው መካተቱ ተጠቁሟል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

 

በሌላ በኩል አዲሱ አሰራር ሰራተኞችን ለማባረር ወይም ለመቀነስ ታቅዶ የቀረበ ነው በሚል ለሚነሱ ትችቶች የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ ምላሽ ሰጥተዋል።


ኮሚሽነሩ እንደተናገሩት የሃገሪቱ ህዝብ ቁጥር 120 ሚሊዮን ሆኖ ሳለ አሁን ያለው የመንግስት ሰራተኛ 2.5 ሚሊዮን ብቻ በመሆኑ የሰራተኛ ቅነሳ የፖሊሲው አላማ አይደለም፤ ዋናው ትኩረት ሰራተኛው የተጣለበትን ሃላፊነትና ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚችልበትን አቅም መገንባት እንደሆነ አስረድተዋል።

 

በጸደቁት ረቂቅ መመሪያዎች መሰረት በሶስቱም የመመዘኛ ዘርፎች ከ90 እስከ 100 በመቶ የሚያመጡ ሰራተኞች የሁለት እርከን የደሞዝ ጭማሪ የሚያገኙ ሲሆን ከ75 እስከ 90 በመቶ ላመጡ ደግሞ የአንድ እርከን ጭማሪ ይደረግላቸዋል።



በተጨማሪም
መመሪያዎቹ የሰው ሃይል እቅድ አዘገጃጀት፣ የደሞዝ ስኬል ማሻሻያ እና አበል አፈጻጸምን የሚያካትቱ ሲሆን የሙያ እጥረት ባለባቸው ዘርፎች ላይ የጋራ ቅጥርን እንደሚፈቅዱም ታውቋል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

93 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።