Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በድጋሚ በነጋዴዎች ተቃውሞ ገጠመው

BS Bethelhem Solomon Jun 16, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 12 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በድጋሚ በነጋዴዎች ተቃውሞ ገጠመው

በተለይም የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ወደ ኋላ 10 ዓመት ተመልሶ እንዲመረመር የሚያዝዘው ድንጋጌ ከፍተኛ ስጋት አዘል ቅሬታዎች ቀርበውበታል

በፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በፓርላማው የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተካሄደው ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ጠንካራ ቅሬታዎች እንደቀረቡበት ተሰምቷል።



ፓርላማው ይፋ ባደረገው የሕዝብ ውይይት ነጋዴዎች ታክስን  ወደ ኋላ 10 ዓመት ተመልሶ መመርመርን ጨምሮ በበርካታ ድንጋጌዎች ላይ ያላቸውን ስጋት በግልጽ ያንፀባረቁ ሲሆን የመንግስት ተወካዮችም ለጥያቄዎቹ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።


በውይይቱ ላይ የንግድ ማህበረሰቡ በተለይም የታክስ ማጭበርበር ወንጀልን ወደ ኋላ 10 ዓመት ተመልሶ እንዲመረመር የሚያዝዘው ድንጋጌ ላይ ከፍተኛ ስጋት አዘል ቅሬታዎች ቀርበዋል።



ተሳታፊዎቹ
እንደገለጹት ሀሰተኛ ደረሰኞችን የሚያረጋግጥ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባልተዘረጋበት ሁኔታ ይህንን ያህል ረጅም ጊዜ ወደ ኋላ ሄዶ ተጠያቂ ማድረግ እና የተጋነነ ቅጣት መጣል ተገቢ አለመሆኑን ተችተዋል።


ከዚህም በተጨማሪ የኔትወርክ መሠረተ ልማት መቆራረጥ ለታክስ ከፋዮች ዋነኛ ማነቆ መሆኑ፣ የታክስ ጉዳዮች በድርድር እንዲፈቱ መደረጉ ለብልሹ አሠራር በር የሚከፍት መሆኑ፣ እንዲሁም ከግብር ተመን ጋር የተያያዙ ችግሮች በውይይቱ ላይ በስፋት ከተነሱ ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።



ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ 10 ዓመት የኋላ ታክስ ምርመራ ድንጋጌ በቀደመው አዋጅ ላይ ምንም ዓይነት የጊዜ ገደብ ባለመቀመጡ ምክንያት የተካተተ እንደሆነ ማስረዳታቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።



የዚህ አዲስ ድንጋጌ ዓላማም የተወሰነ ገደብ ለማስቀመጥ መሆኑን ጠቁመው ከደረሰኝ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቴክኖሎጂ ነክ ችግሮች በቀጣይ አሠራሮችን በማዘመን እንደሚፈቱ ቃል ገብተዋል።


Advertisement
Your ad could be here — contact us

በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ / ያስሚን ወሃብረቢ በበኩላቸው የነባሩ አዋጅ ዕድሜ 10 ዓመት በመሆኑ ከሀገሪቱ የሪፎርም ሥራዎች ጋር እንዲጣጣም ማሻሻያው አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።



አዲሱ ረቂቅ የታክስ ከፋዩን መብትና ግዴታ በግልጽ እንደሚያስቀምጥና የታክስ አስተዳደሩን አገልግሎት እንደሚያቀላጥፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቁመዋል።


በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ የግብር ከፋዩን ችግሮች ለመፍታት ያለመ መሆኑን የተጠቀሰ ሲሆን በተለይም በረቂቁ ላይ የተጠቀሰው "አስማሚ አካል" ገለልተኛና በራሱ አሠራር የሚመራ ሆኖ እንዲቋቋም ቋሚ ኮሚቴው እንደሚሠራ ተገልጿል።


የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ታክስ አስቀድመው ያላሳወቁ ድርጅቶች ምክንያታቸው በአግባቡ ሳይጣራ በቀጥታ ወደ ቅጣት መግባት እንደሌለባቸው እና የይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜም ዳግም እንዲታይ ጠይቀዋል።


የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ አሁን ላይ ያጋጠሙ አንገብጋቢ ችግሮችን ለመፍታት እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሠራበት መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል።



BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

7 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።