Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ያለካሳና ምትክ መሬት ቤታቸውን እንዲለቁ የተጠየቁ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ

BS Bethelhem Solomon Jun 24, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 165 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ያለካሳና ምትክ መሬት ቤታቸውን እንዲለቁ የተጠየቁ ነዋሪዎች ቅሬታ አቀረቡ

ይህ የህግ ጥሰት የማይታረም እና ፍትህ የማይሰጣቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ኢፌድሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ወደ ህዝብ እንባ ጠባቂ እና ወደ ሌሎችም ከፍተኛ የህግ አካላት ይዘው ለማምራት እንደሚገደዱ ነዋሪዎቹ አሳስበዋል።

በሃዋሳ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፊላደልፊያ ቀበሌ ውስጥ በሚገኘውና ታጋይ መንደር በሚል መጠሪያ በሚታወቀው አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች በመንግስት እየተካሄደ ባለው የሀይቅ ዳር የኮሪደር ልማት ሳቢያ ከፍተኛ የህልውና አደጋ እንደተጋረጠባቸው በምሬት ገልጸዋል።


ከሃምሳ
ዓመታት በላይ ቀያቸውን ያቀኑ ትውልድ ያፈሩ እና አካባቢውን በራሳቸው አቅም የገነቡት እነዚህ ዜጎች ልማትን ሰበብ በማድረግ ያለ ምንም ካሳ እና የምትክ መሬት መኖሪያ ቤታችንን እንድንለቅ እየተደረገን ነው ያሉ ሲሆን ግፊቱንም በሰብዓዊ መብት ጥሰትነት እያወገዙት ይገኛሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች እስከ 2000 . ድረስ ለመንግስት የሚጠበቅባቸውን የቦታ ግብር በህጋዊ መንገድ ሲከፍሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።


ይሁን
እንጂ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያለምንም ግልጽ ምክንያት ግብር እንዳይከፍሉ መታገዳቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎቹ  ከተማዋ ስትሰፋ እና ለሌሎች አካባቢዎች የካርታ ፕላን ሲዘጋጅላቸው እነርሱም ተመሳሳይ ህጋዊ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ከአስተዳደሩ ሲሰጣቸው የነበረው ምላሽ ግን አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል እንደነበር በምሬት ይናገራሉ።

ችግሩ ይበልጥ የተባባሰው በቅርቡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ የልማቱ አካል የሆነውን የኮሪደር ስራ ምክንያት በማድረግ የአካባቢው አመራሮች ነዋሪዎቹ በአጭር ቀናት ውስጥ በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የቃል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ተናግረዋል።


ከዚህም
ባለፈ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አመራሮች በመካከላችሁ አቅም ያላቸው ነዋሪዎች ስላሉ ገንዘብ በማዋጣት አቅም ለሌላቸው የሁለት ወር የቤት ኪራይ ክፈሉ ማለታቸውን እማኞች አስታውቀዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ነዋሪዎቹ የከተማዋን ልማትም ሆነ የሀይቅ ዳር ፕሮጀክቱን እንደማይቃወሙ እና እንዲያውም እንደሚደግፉ በግልጽ አስታውቀው ነገር ግን ማንኛውም የልማት ስራ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት፣ ክብር እና የንብረት ባለቤትነት ህግን በተከተለ መልኩ መከናወን እንዳለበት አጥብቀው አሳስበዋል።


ኢትዮጵያ
የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና የኢፌድሪ ህገ-መንግስት የዜጎችን የንብረት መብት በግልጽ ያረጋገጡ መሆናቸውን የተገለጸ ሲሆን  የህዝብ መሬት ለልማት ሲወሰድ በቅድሚያ ማሳወቅ፣ ፍትሃዊ ካሳ መክፈል እና ምቹ የመቀየሪያ ቦታ መስጠት አስፈላጊ መሆኑ በአዋጅ በግልጽ እንደተቀመጠ የህግ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ነገር ግን አግባብነት ላላቸው አስተዳደራዊ ቢሮዎች በተለያዩ ወራት ተደጋጋሚ የቅሬታ ደብዳቤዎች ቢገቡም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ተገቢ ግልጽ እና ህጋዊ ምላሽ አልተሰጠም ተብሏል።


በመሆኑም ማህበረሰቡ ይህ አስተዳደራዊ በደል በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የከተማዋ ከንቲባ በአካል ተገኝተው ህዝቡን እንዲያወያዩ እና በህጉ መሰረት የካሳ እና የምትክ ቦታ ዝግጅት እንዲደረግላቸው አጥብቀው ጠይቀዋል።

ይህ የህግ ጥሰት የማይታረም እና ፍትህ የማይሰጣቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ኢፌድሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ወደ ህዝብ እንባ ጠባቂ እና ወደ ሌሎችም ከፍተኛ የህግ አካላት ይዘው ለማምራት እንደሚገደዱ ነዋሪዎቹ  አሳስበዋል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

18 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።