በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋን ሳይንሳዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመምራት የተዘጋጀ መተመኛ ጥናት ለፓናል ውይይት ቀርቧል።
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ እና የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በጋራ ያከናወኑት ይህ አዲስ የዋጋ መተመኛ ጥናት ከሚቀጥለው 2019 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ታውቋል።
በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ጫናን ለመቀነስና በቤት ኪራይ ገበያው ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ህገ-ወጥና ዘፈቀዳዊ አሰራሮችን ለመግታት በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ቢሮው በ2016 ዓ.ም ሰፊ የአከራይና ተከራይ ውል ምዝገባ ማከናወኑን ያስታወሱት ኃላፊዋ ይህም በዘርፉ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ያልተገቡ አሰራሮችን ያስቀረ ትልቅ ስኬት እንደነበር ገልጸዋል።
በአዋጁ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት የተዘጋጀው ይህ የዋጋ መተመኛ ጥናት የውል ማደስ ሂደትን ፍትሃዊ፣ ሳይንሳዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመምራት ያለመ ነው።
ያለአግባብና በየጊዜው የሚጨምር የቤት ኪራይ ዋጋ የዜጎችን የመክፈል አቅም በማዳከም ለዋጋ ንረት መባባስ አንድ ምክንያት በመሆኑ ጥናቱ በመዲናዋ ሁለንተናዊ እሴቶች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ተብራርቷል።
ጥናቱ አከራዩ ከንብረቱ የወቅቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ ፍትሃዊ ገቢ እንዲያገኝ የሚያረጋግጥ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ተከራዩ ከገቢው ጋር የተመጣጠነ ኪራይ በመክፈል የተረጋጋ የኢኮኖሚ ህይወት እንዲመራ ያደርጋል።
ይህ የቤት ኪራይ ገበያውን ጤናማና ሊተነበይ የሚችል በማድረግ የከተማዋን የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደሚያረጋጋ እና ቤተሰቦች በተደጋጋሚ ቤት ከመቀየር ስጋት እንደሚታደጋቸው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ግልጽና ህጋዊ አሰራርን በመዘርጋት በአከራይና ተከራይ መካከል የነበረውን ያለመተማመን መንፈስ ከመቅረፍ ባለፈ የደላሎችና የህገ-ወጥ ደላሎችን ጣልቃ ገብነት እንደሚያስቀር አመልክተዋል።
ዛሬ የቀረበው የዋጋ ትመና ጥናት በዘፈቀደ የተሰራ ሳይሆን የከተማዋን ነዋሪ የመክፈል አቅም መሰረት ያደረገ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።
በዛሬው ዕለት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ የመኖሪያ ቤት አከራዮች እና ተከራዮች ተሳትፈዋል።
የአከራይና ተከራይ ግንኙነትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እና በዘርፉ የሚታዩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በተጀመረው የዲጂታል ምዝገባ ሂደት እስካሁን ወደ አምስት መቶ ሺህ የሚጠጉ ቤቶች ወደ ሲስተሙ መግባታቸውን ቢሮው ቀደም ብሎ ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚህም መንግሥት በየዓመቱ አንድ ጊዜ የከተማዋን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ የገበያ ጥናት ካካሄደ በኋላ የገበያ ዕድገት መኖሩ ሲረጋገጥ በየዓመቱ ሰኔ 30 ላይ በሚያወጣው ይፋዊ መግለጫ መሠረት የዋጋ ጭማሪውን በፐርሰንት (በመቶኛ) ይወስናል።
በተጨማሪም አብዛኞቹ ውሎች ጊዜያቸው የሚያበቃው ከሰኔ 30 በኋላ በመሆኑ በውል ስምምነት ውስጥ እያሉ ዋጋ መጨመር ፈጽሞ እንደማይፈቀድም በወቅቱ አጽንኦት ተሰጥቶ ነበር።