Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

መንግሥት አዳዲስ የታክስ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ ተሰማ

BS Bethelhem Solomon Jul 17, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 666 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
መንግሥት አዳዲስ የታክስ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ ተሰማ

ከታቀዱት ማሻሻያዎች መካከል በዋነኝነት የተቀመጠው የነዳጅ ድጎማን ሙሉ በሙሉ ማንሳት እንደሆነ ሪፖርቱ አሳይቷል።



የኢትዮጵያ
መንግሥት የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማስቀጠል 2019 በጀት ዓመት 5 ቢሊዮን ዶላር አዲስ የውጭ ብድር ለመውሰድ ማቀዱንና በቀጣዮቹ ወራት አዳዲስ የታክስ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ይፋዊ ሪፖርት አስታውቋል።



መንግሥት ከታክስ የሚገኘውን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግና ማንኛውንም ድጎማ ለማንሳት ቃል መግባቱን የጠቆመው የገንዘብ ተቋሙ፤ በኢኮኖሚው ላይ ተግባራዊ የሚደረጉ ቁልፍ እርምጃዎችን በዝርዝር አስቀምጧል።



ከታቀዱት ማሻሻያዎች መካከል በዋነኝነት የተቀመጠው የነዳጅ ድጎማን ሙሉ በሙሉ ማንሳት እንደሆነም ሪፖርቱ አሳይቷል።



በዚህም 2019 በጀት ዓመት የነዳጅ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን የሚደረግ ሲሆን ከነዳጅ ምርቶች ላይ ብቻ በድምሩ 176 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገልጿል።



ይህ ገቢ 93 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ 80 ቢሊዮን ብር ኤክሳይስ ታክስ እና 3 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ ካልሆነ የሀገር ውስጥ ታክስ የሚሰበሰብ ይሆናል።


በዚህም የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ የካፒታል አቅም 286 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ በማድረግ የነዳጅ ግዥ ክፍያዎችን በቀጥታ ለአቅራቢዎች መክፈል የሚያስችል አዲስ የግዢ ስርዓት ተግባራዊ ይደረጋል።


Advertisement
Your ad could be here — contact us

በተጨማሪም ለኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሲሰጡ የነበሩ የታክስ ነፃ መብቶች ወደ መደበኛ ታክስ ይሚቀየሩ ሲሆን እስከ ታኅሣሥ 2019 . ድረስ በሚተገበሩ አዳዲስ አሰራሮች በአልኮል፣ በትምባሆ እና በተሽከርካሪ ባለቤትነት ላይ አዲስ የኤክሳይስ ታክስ ተመን ተግባራዊ ይሆናል።



ከዚህም ባሻገር በትላልቅ ከተሞች የንብረት ዋጋ ትመና እየተካሄደ ሲሆን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 0.3 በመቶ ታክስ ለመሰብሰብ የሪል ስቴት እና የንብረት ታክስ ስርዓት እየተዘጋጀ ነው ተብሏል



በተጨማሪም መንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፋማነት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና ለሕዝብ ጥቅም የሚሰሩ ስራዎች ካሉ በመንግሥት በጀት እንዲካካሱ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።


የውጭ ብድርን በተመለከተ መንግሥት ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ማስፈጸሚያ ከሚያቅደው 5 ቢሊዮን ዶላር አዲስ ብድር ውስጥ አብዛኛው ዝቅተኛ ወለድ ያለው ቢሆንም፤ ለኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ ብቻ 950 ሚሊዮን ዶላር የንግድ ብድር እንዲወሰድ ስምምነት ተደርጓል።



ይህ እርምጃ ከቀድሞው ቃል ኪዳን በተለየ ሁኔታ የተፈቀደ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የዩሮ ቦንድን ጨምሮ ከሁሉም የውጭ አበዳሪዎች ጋር እስከ ታኅሣሥ 2019 . ድረስ የእዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ ለመድረስ መንግሥት እየሰራ ነው ተብሏል


ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 10.2 በመቶ እያደገ መሆኑ ቢገለጽም የአይ ኤም ኤፍ ሪፖርት የዚህን የታክስ እና የዋጋ ማስተካከያ በሕዝቡና በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ማኅበራዊ ጫና በተመለከተ በዝርዝር አላስቀመጠም።



ይልቁንም በሀገር ውስጥ ግጭቶች መባባስ፣ በጎረቤት አገራት አለመረጋጋት እና በዓለም አቀፍ የገበያ አቅርቦት ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች ለታቀዱት ለውጦች ዋና ዋና ስጋቶች መሆናቸውን የሪፖርቱ ግምገማ ያሳያል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

52 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።