የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ለማስቀጠል በ2019 በጀት ዓመት 5 ቢሊዮን ዶላር አዲስ የውጭ ብድር ለመውሰድ ማቀዱንና በቀጣዮቹ ወራት አዳዲስ የታክስ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ይፋዊ ሪፖርት አስታውቋል።
መንግሥት ከታክስ የሚገኘውን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግና ማንኛውንም ድጎማ ለማንሳት ቃል መግባቱን የጠቆመው የገንዘብ ተቋሙ፤ በኢኮኖሚው ላይ ተግባራዊ የሚደረጉ ቁልፍ እርምጃዎችን በዝርዝር አስቀምጧል።
ከታቀዱት ማሻሻያዎች መካከል በዋነኝነት የተቀመጠው የነዳጅ ድጎማን ሙሉ በሙሉ ማንሳት እንደሆነም ሪፖርቱ አሳይቷል።
በዚህም በ2019 በጀት ዓመት የነዳጅ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን የሚደረግ ሲሆን ከነዳጅ ምርቶች ላይ ብቻ በድምሩ 176 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገልጿል።
ይህ ገቢ ከ93 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከ80 ቢሊዮን ብር ኤክሳይስ ታክስ እና ከ3 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ ካልሆነ የሀገር ውስጥ ታክስ የሚሰበሰብ ይሆናል።
በዚህም የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝ የካፒታል አቅም በ286 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ በማድረግ የነዳጅ ግዥ ክፍያዎችን በቀጥታ ለአቅራቢዎች መክፈል የሚያስችል አዲስ የግዢ ስርዓት ተግባራዊ ይደረጋል።
በተጨማሪም ለኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሲሰጡ የነበሩ የታክስ ነፃ መብቶች ወደ መደበኛ ታክስ ይሚቀየሩ ሲሆን እስከ ታኅሣሥ 2019 ዓ.ም ድረስ በሚተገበሩ አዳዲስ አሰራሮች በአልኮል፣ በትምባሆ እና በተሽከርካሪ ባለቤትነት ላይ አዲስ የኤክሳይስ ታክስ ተመን ተግባራዊ ይሆናል።
ከዚህም ባሻገር በትላልቅ ከተሞች የንብረት ዋጋ ትመና እየተካሄደ ሲሆን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 0.3 በመቶ ታክስ ለመሰብሰብ የሪል ስቴት እና የንብረት ታክስ ስርዓት እየተዘጋጀ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም መንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፋማነት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና ለሕዝብ ጥቅም የሚሰሩ ስራዎች ካሉ በመንግሥት በጀት እንዲካካሱ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
የውጭ ብድርን በተመለከተ መንግሥት ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ማስፈጸሚያ ከሚያቅደው 5 ቢሊዮን ዶላር አዲስ ብድር ውስጥ አብዛኛው ዝቅተኛ ወለድ ያለው ቢሆንም፤ ለኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ ብቻ 950 ሚሊዮን ዶላር የንግድ ብድር እንዲወሰድ ስምምነት ተደርጓል።
ይህ እርምጃ ከቀድሞው ቃል ኪዳን በተለየ ሁኔታ የተፈቀደ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የዩሮ ቦንድን ጨምሮ ከሁሉም የውጭ አበዳሪዎች ጋር እስከ ታኅሣሥ 2019 ዓ.ም ድረስ የእዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ ለመድረስ መንግሥት እየሰራ ነው ተብሏል።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ10.2 በመቶ እያደገ መሆኑ ቢገለጽም የአይ ኤም ኤፍ ሪፖርት የዚህን የታክስ እና የዋጋ ማስተካከያ በሕዝቡና በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ማኅበራዊ ጫና በተመለከተ በዝርዝር አላስቀመጠም።
ይልቁንም በሀገር ውስጥ ግጭቶች መባባስ፣ በጎረቤት አገራት አለመረጋጋት እና በዓለም አቀፍ የገበያ አቅርቦት ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ተግዳሮቶች ለታቀዱት ለውጦች ዋና ዋና ስጋቶች መሆናቸውን የሪፖርቱ ግምገማ ያሳያል።