Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ቅጣት ሊጣል ነው

BS Bethelhem Solomon Aug 28, 2026 Updated 3h ago 1 ደቂቃ ንባብ 417 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ቅጣት ሊጣል ነው

አሽከርካሪው ተመሳሳይ ጥፋት ደጋግሞ ከተገኘ ደግሞ እስከ ሥራ ማገድ የሚደርስ ከባድና ጥብቅ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሏል።


የአዲስ
አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ እየተስተዋለ ያለውን ህገ-ወጥ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ፣ የመስመር ማሳጠር እና ህዝብን የማማረር ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ አጠቃላይ አስተዳደራዊ እና የህግ ማዕቀፍ እርምጃዎችን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቋል።


ቢሮው ህብረተሰቡን ከሚገባቸው ውጪ ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ እንዲሁም ህግን በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ እስከ 5 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣትና ተደጋጋሚ ጥፋት ሲፈጸምም እስከ ስራ ማገድ የሚደርሱ ጥብቅ ውሳኔዎችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።


የህዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ ጥናቶችን በማካሄድና በማስወሰን ረገድ የበኩሉን ሃላፊነት እየተወጣ የሚገኘው ቢሮው የታሪፎች መሬት ላይ መውረድና ትክክለኛ ተግባራዊነት በቅርበትና ያለማቋረጥ እየተቆጣጠረ እንደሚገኝ የቢሮው የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው አብራርተዋል።


በከተማ አቀፍ ደረጃ 15 ሺህ በላይ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች በየቀኑ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ሲሆን አብዛኛው አሽከርካሪ በህጋዊ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም የተወሰኑ አካላት ግን ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ህብረተሰቡን ሲያማርሩ እንደሚስተዋሉ ተረጋግጧል።


ይህንን ህገ-ወጥ አሰራር ለመቆጣጠር በተደረገው ርብርብም ባለፈው የበጀት ዓመት ብቻ ህግ በተላለፉ 120 ሺህ በላይ የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው አስተዳደራዊና የህግ እርምጃ መወሰዱ ተመላክቷል።


ከእነዚህ አሽከርካሪዎች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ከሚገባው በላይ የታሪፍ ጭማሪ አድርገው ሲያስከፍሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሰፊ ድርሻ የሚይዙት አሽከርካሪዎች ደግሞ መስመር በማሳጠር፣ ከተፈቀደው የመቀመጫ ወንበር በላይ በመጫን እና ከተያያዥ የትራንስፖርት ህግ ጥሰቶች ጋር ተያይዞ የተመዘገቡባቸው ናቸው ተብሏል

የቢሮው ሃላፊ አክለው እንደገለጹት የሚወሰደው እርምጃ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ የገንዘብ ቅጣት ብቻ ሳይሆን የጥፋቱ ክብደት እየታየ የሚቀጥል ነው።


በዚህም መሰረት ጥፋተኞች እንደ ጥፋታቸው ደረጃ እስከ 5 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት የሚጣለባቸው ሲሆን አሽከርካሪው ተመሳሳይ ጥፋት ደጋግሞ የተገኘ ከሆነ ደግሞ እስከ ሥራ ማገድ የሚደርስ ከባድና ጥብቅ ውሳኔዎች እየተወሰኑባቸው ይገኛል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ይህንን ችግር በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡ ተሳትፎ በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ የቅንጅት ስራዎችን መዘርጋቱን ያስታወቀው ቢሮው ህብረተሰቡ ከታሪፍ በላይ እንዳይጠየቅና እንግልት እንዳይገጥመው ከመነሻ ተርሚናል ተገቢውን ህጋዊ ክፍያ ከፍሎ በመውጣት የራሱን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል።


ከዚህም ባሻገር ማንኛውም ህገ-ወጥ የታሪፍ ጭማሪ፣ መስመር ማሳጠር ወይም ህግን የጣሰ አሰራር ሲያጋጥመው ህብረተሰቡ የተሸከርካሪውን የሰሌዳ ቁጥር እና የተሳፈረበትን መስመር በመያዝ በነፃ የጥቆማ መስመር 9417 በመደወል አፋጣኝ ጥቆማ እንዲሰጥ የትራንስፖርት ቢሮ ጥሪውን አስተላልፏል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

80 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።