የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትናንትናው እለት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ታሪካዊ ድምጽ አሰጣጥ፤ አህጉራት በሉል ላይ ያላቸውን እውነተኛ እና ተጨባጭ የመሬት ስፋት የሚወክለው አዲስ የዓለም ካርታ በአብላጫ ድምፅ አጸደቀ።
በዚህም እውነተኛው የአፍሪካ ካርታ ግዙፍነት አሜሪካን፣ ቻይናን፣ ሕንድን፣ ጃፓንን፣ ሜክሲኮን እና አብዛኛውን አውሮፓን በአፍሪካ ውስጥ ከቶ አሁንም ተጨማሪ መሬት ማስቀረት የሚችል ያህል ነው ተብሏል።
የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት እና በኒውዮርክ የሚገኘው የአፍሪካ ቡድን በጋራ ባቀረቡት ካርታውን ማስተካከል በሚለው በዚህ የውሳኔ ሃሳብ ላይ 164 ሀገራት ድምፃቸውን ሲሰጡ ስድስት ሀገራት ድምፅ ከመስጠት ተቆጥበዋል፤ አሜሪካ ብቻ ውሳኔውን በመቃወም ተቃውሟዋን አሰምታለች።
ውሳኔውን በቶጎ ሪፐብሊክ አቅራቢነት እና በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፎሬ እሶዚምና ኛሲንግቤ ቁርጠኝነት የተመራ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ውሳኔ በአውሮፓውያኑ 1569 በአውሮፓዊው ኬፕቶግራፈር ጄራርደስ መርኬተር ለባህር ንግድ አሰሳና ለመርከብ ጉዞዎች መመሪያ እንዲሆን ተብሎ የተሠራውን እና ለዘመናት አፍሪካን፣ ላቲን አሜሪካንና ደቡብ እስያን እጅግ አነስተኛ አድርጎ ሲያሳይ የነበረውን አሰራር ያስወግዳል።
በምትኩ አህጉራት በትክክለኛው አንጻራዊ መጠናቸው እንዲታዩ የሚያስችለውን እና በካርታ ባለሙያዎች እ.አ.አ በ2018 የተዋወቀውን “ኢኳል ኤርዝ ፕሮጀክሽን” ካርታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተካ ይጠይቃል።
ለዘመናት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው የሜርካቶር አሰራር ባለ ሶስት ዲማንሽን የሆነውን ሉል ወደ ጠፍጣፋ ወረቀት በመቀየር ሂደት አውሮፓን፣ ሰሜን አሜሪካን እና ራሽያን በማዕከልነት እና በግዙፍነት በመሳል የአውሮፓውያንን የበላይነት ሲያንጸባርቅ ቆይቷል።
ለማሳያ ያህልም በነባሩ ካርታ ላይ ግሪንላንድ ከአፍሪካ አህጉር ጋር እኩል ስፋት እንዳላት ሆና ትሳል የነበረ ቢሆንም፤ በእውነታው ግን አፍሪካ ከግሪንላንድ በ14 እጥፍ የምትበልጥ እና ግሪንላንድም በስፋቷ ከኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር እኩል የሆነች ሀገር መሆኗ ተመላክቷል።
የባለሙያዎች ቡድን አባል የሆኑት ቦጃን ሳቭሪክ Equal Earth ካርታ የአህጉራትን አንጻራዊ የገጽታ ስፋት ፍጹም በሆነ መልኩ እንደሚጠብቅ አስረድተዋል።
ውሳኔውን በቀዳሚነት ያስጀመረችው የቶጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮበርት ዱሴ “ካርታዎች የሰዎችን አስተሳሰብ፣ የትምህርት ስርዓት እና የትውልድ አመለካከት በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው፤ በጭራሽ ገለልተኛ አይደሉም” በማለት የተዛባ የፕላኔታችን ምስል በትውልዶች መካከል መተላለፉ ተገቢ አለመሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ አዲሱ ውሳኔ መጽደቅ የደቡባዊውን ዓለም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች እንዲሁም የልማት አቅሞች ዝቅ አድርጎ የሚያሳይ ታሪካዊ ስህተት የሚያርም ትልቅ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የትምህርት ሥርዓቶች፣ አታሚዎች እና የዲጂታል አቅራቢዎች አዲሱንና ትክክለኛውን የካርታ ምስል ደረጃ በደረጃ ሥራ ላይ እንዲያውሉትም ጥሪ አቅርበዋል።
ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ ሀገራት አዲሱን ካርታ ለመተግበር ቁርጠኝነታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ፈረንሳይ የሜርካቶርን ካርታ ሙሉ በሙሉ እንደምትተው አስታውቃለች።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን-ኖኤል ባሮ “ካርታ መቀየር ብቻውን ዓለምን አይለውጠውም፤ ነገር ግን ለዘመናት የቆየ የተዛባ ውክልና ማስተካከል ራሱ ትልቅ የእውነት እርምጃ ነው” ብለዋል።