Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ከምሽቱ 4 ሰዓት በፊት ሱቃቸውን የሚዘጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ተባለ

BS Bethelhem Solomon Aug 5, 2026 2 ደቂቃ ንባብ 93 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ከምሽቱ 4 ሰዓት በፊት ሱቃቸውን የሚዘጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ተባለ

በመዲናዋ አጠቃላይ የምሽት ንግድ ሥርዓቱን ባልተከተሉ እና ሕጉን ጥሰው በተገኙ ከ1 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱም ተገልጿል።


በአዲስ አበባ ከተማ ካለው የሸማቾች ፍላጎትና ከተማዋ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ አንጻር የንግድ ተቋማት ከምሽቱ 4 ሰዓት በፊት እንዳይዘጉ የተላለፈውን ትዕዛዝ በመተው አስቀድመው በሚዘጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ።

የንግድ ተቋማት አገልግሎታቸውን እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ እንዲሰጡ የተደረገው የኅብረተሰቡን የትራንስፖርትና የፍላጎት እንቅስቃሴ ለማሳለጥ እንዲሁም የሥራ ባህልን ለማዳበር ታስቦ ቢሆንም አንዳንድ ነጋዴዎች ይህንን ሕግ ባለማክበር ሰዓት ሳይደርስ ሱቆቻቸውን እየዘጉ እንደሚገኙ ተነግሯል።

ይህን ህገወጥ ተግባር ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት ከተማ አቀፍ ተቋማትና የክፍለ ከተማ የንግድ ጽሕፈት ቤቶች ተቀናጅተው ጠንካራ ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የምሽት ንግድ በማያከናውኑ እና ሕጉን በሚተላለፉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ተደርጎ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የገለጹት የክፍለ ከተማው የንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ዘነበ ናቸው።

ኃላፊው አክለውም እስካሁን ባለው ሂደት በ18 በሚደርሱ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል። የምሽት ንግድ ልማድ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሥራ ሰዓት የሚስማማ መሆኑን ገልጸው የሥራ ባህልን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለውም አስገንዘብተዋል።


በተመሳሳይ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ቢሰጠኝ በበኩላቸው የምሽት ንግድ ሥርዓት እንዲለመድ ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የሰዓት ገደቡ መጀመሪያ ሲወጣ ለነጋዴዎች ሊሟሉላቸው የሚገቡ አንዳንድ ክፍተቶች እንደነበሩ ያነሱት ኃላፊው አሁን ላይ ግን የምሽት የትራንስፖርት አገልግሎት ጭምር እንዲመቻች መደረጉን ገልጸዋል። በመሆኑም ደንብ በሚጥሱ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው የማስተካከያ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው አሁን ላይ በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሰፊ እንደሆኑ ጠቁመዋል። በርካታ ተቋማት የሥራ መውጫ ሰዓታቸው እስከ ምሽት የሚዘልቅ በመሆኑ፣ ነጋዴዎች ኅብረተሰቡን እስከ ተገለጸው ሰዓት ድረስ የማገልገል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በመዲናዋ አጠቃላይ የምሽት ንግድ ሥርዓቱን ባልተከተሉ እና ሕጉን ጥሰ በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ እስከ አሁን ድረስ ከ1 ሺህ በላይ በሚሆኑት ላይ እርምጃ መወሰዱን የገለጹት ወ/ሮ ሀቢባ የምሽት ንግድን በተመለከተ የወጡ ደንቦችን ሙሉ በሙሉ ለማስፈጸም የቁጥጥር ሥራው አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስበዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባወጣው  የምሽት ንግድና ትራንስፖርት ደንብ መሰረት ሁሉም ንግድ ቤቶች ከምሽቱ 12፡00 እስከ 4 ሰዓት ድረስ በግዴታ ክፍት መሆን እንዳለባቸው መወሰኑ ይታወሳል።

በዚህም በሩን ዘግተው የሚሰሩ ተቋማትም ክፍት መሆናቸውን የሚያሳይ የኤሌክትሪክ ምልክት ማሳየት የሚጠበቅባቸው ሲሆን በቀን ሲቀርቡ የነበሩ ሸቀጦችና አገልግሎቶች በተሟላ ሁኔታ መቅረብ እንዳለባቸው ደንቡ ያስገድዳል። 

እንዲሁም በመንገድ ዳር የሚገኙ ተቋማት ከምሽት 12፡00 እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ የውጭና የውስጥ መብራቶቻቸውን የማብራት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
እነዚህን ሕጎች በመተላለፍ ከተቀመጠው ሰአት በፊት መዝጋት፣ እያለ የለም ማለት፣ መብራት አለማብራት ወይም በታሪፍ በላይ ማስከፈል ሲፈጸም የ10,000 እና የ5,000 እስከ 7,000 ብር ቅጣት ያስከትላል። 

ጥፋቱ ሲደጋገም ቅጣቱ እየጨመረ የሚሄድ ሲሆን ሁኔታውን ማስተካከል ካልተቻለ የንግድ ሥራ ፈቃድ እስከ ማገድና መሰረዝ እንዲሁም የመንግስት የኪራይ ቤት ውል እስከ ማቋረጥ የሚደርስ ጥብቅ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በደንቡ ሰፍሯል። 

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

60 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።