Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

ከ36 የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች ጋር ሕገ-ወጥ የኃይል ሽያጭ ውል የፈፀሙ ከፍተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወሰደ

BS Bethelhem Solomon Aug 6, 2026 2 ደቂቃ ንባብ 151 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ከ36 የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች ጋር ሕገ-ወጥ የኃይል ሽያጭ ውል የፈፀሙ ከፍተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወሰደ

በተለያየ ዘርፍ ያሉ በርካታ የመንግስት አመራሮች እና ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱም ተነግሯል

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተገቢው መመሪያ በሌለበት ሁኔታ ከ36 የዳታ ማይኒንግ ድርጅቶች ጋር ሕገ-ወጥ የኃይል ሽያጭ ውል የፈጸሙ 4 ከፍተኛ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን የመንግስት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል። 

 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ ዛሬ ሐምሌ 30፤ 2018 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሀገሪቱን ከምታሳየው እድገት ባሻገር “ሕገ-ወጥነት እና የሙስና ተግባራት የልማቱ ዋነኛ ፈተና” ሆነው ቆይተዋል ብለዋል። 

Advertisement
Your ad could be here — contact us

 

ድርጊቱ የመንግሥት መዋቅርን ጨምሮ በንግዱ ማኅበረሰብ፣ በልማት ድርጅቶች፣ በግለሰቦች እና በተገልጋዮች በተደራጀ መንገድ ተስፋፍቷል ሲሉ ሚኒስትሯ አክለዋል። 

 

በዚህም  በተለያየ ዘርፍ ያሉ በርካታ የመንግስት አመራሮች እና ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።

 

እርምጃ ከተወሰደባቸው ዘርፎች ቤቲንግ እና ፊንቴክ ቢዝነሶች፣ ማዕድን ዘርፍ ሕገ-ወጥ ዝውውር፣ ከነዳጅ አቅርቦት እና ሎጂስቲክስ፣ አፈር ማዳበሪያ ግዢ፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ዘርፍ እና ህገ ወጥ የስራ ስምሪት እና ዝውውር ተካተዋል።


  
ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በሐዋላ እና በጥቁር ገበያ ተሳታፊ የሆኑ 169 ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ዜጎች በሕግ ተጠያቂ ተደርገዋል። 

 

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የሰዎች ዝውውር የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ሲስተምን በማዛባት እና ጉቦ በመቀበል ወንጀል የተሳተፉ 8 ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል። 

 

44 ደላሎች እና አዘዋዋሪዎችም እንዲሁ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሕገ-ወጥ ፈቃድ የነበራቸው ተቋማት ሙሉ በሙሉ ታሽገዋልብሏል።

 

በገቢዎችና ጉምሩክ ዘርፍ የግብር ውሳኔዎችን በመቀነስ፣ ሐሰተኛ ደረሰኞች በማወራረድ፣ እና በሲስተም መረጃ በማጥፋት የመንግሥት ገቢን በማሳጣት በራሳቸው፣ በዘመድ እና በሹፌሮቻቸው አካውንት በመጠቀም የጥቅም ትስስር የፈጠሩ 91 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል። 

 

ከንግድ ባንክ ደንበኞች አካውንት ላይ በማጭበርበር ገንዘብ የወሰዱ 36 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የባንክ ሒሳባቸው እንዲታገድ የተደረገ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ለሕገ-ወጥ ዝውውር ሽፋን ይሰጡ ነበሩ የተባሉ 7 የክሪፕቶ ካረንሲ መተግበሪያዎች በሀገር ውስጥ እንዳይሠሩ ሙሉ በሙሉ መታገዳቸውን አስታውቋል። 

 

በአፈር ማዳበሪያ ግዢ አሻጥር የግብርና ሚኒስቴር አመራሮች ላይ የወንጀል ተጠያቂነት እርምጃ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ የሽፋን ደብዳቤዎችን በማዘጋጀት፣ ነዳጅ በመደበቅ እና አየር በአየር በመሸጥ ወንጀል የተሳተፉ 38 የመንግሥት አመራሮች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል ሲል መግለጫው አካቷል።

 

ምርት ልከው የውጭ ምንዛሬ ተመላሽ ያላደረጉ 29 ላኪ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች በተጨማሪ የወርቅ ምርትን ከገበያ ውጭ በኮንትሮባንድ በማስወጣት ወንጀል የተሳተፉ የመንግሥት ኃላፊዎችን፣ የፀጥታ መዋቅር አመራሮችን፣ አምራቾችን እና የውጭ ዜጎችን ጨምሮ 183 ግለሰቦች በሕግ ተጠያቂ መደረጋቸው ተገልጿል። 

 

ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ በነበሩ ከ7 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶችና መጋዘኖች ላይ የማሸግ እርምጃ እንዲሁም መንግሥትን ግብር ያጭበረበሩ፣ ገቢያቸውን የሰወሩ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በፈጸሙ 38 የቤቲንግ ድርጅቶች ባለቤቶች በቁጥጥር ስር በማዋል የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ ማድረጉንም አገልግሎቱ አስታውቋል። 

 

ሚኒስትሯ የተጀመረዉ እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን ማኅበረሰቡ ሙስናን በማጋለጥ፣ ሕጋዊ መብቱን በመደለያ ባለመጠየቅ እና ከሕገወጦች ጋር ባለመተባበር ከመንግሥት ጎን በመቆም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

62 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።