Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

100,000 ብር ቅጣት እና የንግድ ፈቃድ ስረዛ የሚያስከትለው አዲሱ የደህንነት ደንብ ሊተገበር ነው

BS Bethelhem Solomon Aug 7, 2026 Updated 3h ago 1 ደቂቃ ንባብ 82 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
100,000 ብር ቅጣት እና የንግድ ፈቃድ ስረዛ የሚያስከትለው አዲሱ የደህንነት ደንብ ሊተገበር ነው

በተጨማሪም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያላስተካከሉ ተቋማት የንግድና ስራ ፈቃዳቸው እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ ይደረጋል ተብሏል።


በአዲስ
አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የህንፃዎች ከፍታ፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና የህዝብ ቁጥር እድገት ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና የህይወትና ንብረት ደህንነትን ለማረጋገጥ የወጡት የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ ቁጥር 132/2014 እና መመሪያ ቁጥር 163/2017 ወደ ሙሉ ትግበራ ሊገቡ መሆናቸው በይፋ ተገለጸ።

በዚህም ተቋማትና የህንፃ ባለቤቶች አስፈላጊዎቹን የደህንነት መስፈርቶች ሳያሟሉ ቢገኙ ከብር 10,000.00 እስከ ብር 100,000.00 የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣል ተገልጿል።

በተጨማሪም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያላስተካከሉ ተቋማት የንግድና ስራ ፈቃዳቸው እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ የሚያደርገው ይህ ጥብቅ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሐመድ በመግለጫቸው እንዳስገነዘቡት የዚህ ደንብና መመሪያ ዋና ዓላማ በከተማዋ ውስጥ አደጋ እንዳይደርስ አስቀድሞ መከላከል ነው።

ከዚህ ቀደም አደጋ ከደረሰ በኋላ ይደረግ የነበረውን የኋላቀር ምላሽ ሰጪ የመከላከል ተግባር ሙሉ በሙሉ ቀይሮ፤ አስቀድሞ በዝግጅትና በቅኝት አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር መሆኑንም አብራርተዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ኮማንደር አህመድ አያይዘውም ይህ መመሪያ ተፈጻሚ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሰን ውስጥ ብቻ መሆኑን በመጠቆም፤ ተቋሙ በከተማዋ የሚገኙ ተቋማትን የሙያና የቴክኒክ ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ የፍተሻና ቁጥጥር ስራ በማካሄድ የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጥ መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል።

በወጣው አዲስ ደንብና መመሪያ መሠረት ማንኛውም የህዝብ መገልገያ ህንፃ፣ የንግድ ተቋም ወይም አደገኛ ንጥረ ነገሮችን የሚያከማች ድርጅት በየዓመቱ ከአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመያዝ እና የማደስ ሕጋዊ ግዴታ ተጥሎበታል።

ይህን ተከትሎ ተቋማትና የህንፃ ባለቤቶች ደረጃውን የጠበቀ የውሃ መቅጃ ሀይድራንት (Hydrant) የእሳት ማጥፊያ ሲሊንደሮች፣ የጭስ ማወቂያዎችና የስፕሪንክለር ስርዓት የመገጠም እንዲሁም በህንፃ ዲዛይኖቻቸው ውስጥ የአደጋ ጊዜ ማምለጫ መንገዶችን የማካተት ጥብቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው ደንብና መመሪያውን በተመለከተ ለህብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።


ከዚህም በተጨማሪ ህጉን ሳያውቁ የሚቀሩ አካላት እንዳይኖሩ ከተደረገ በኋላ ደንቡንና መመሪያውን ዐውቀውም ሆነ ሳያውቁ ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በጥብቅ እንደሚወሰዱ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

63 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።