Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

የአሽከርካሪዎችን የጡረታና የሥራ ውል መብት የሚያስከብር ስምምነት ተደረገ

BS Bethelhem Solomon Sep 2, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 426 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የአሽከርካሪዎችን የጡረታና የሥራ ውል መብት የሚያስከብር ስምምነት ተደረገ

ይህ ስምምነት የዘርፉን አሽከርካሪዎች የሥራ ውልና የማኅበራዊ ዋስትና መብቶች ሙሉ በሙሉ የሚያስከብር መሠረት የሚጥል መሆኑ ተገልጿል።


በኢትዮጵያ
አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች መደበኛ እና ሕጋዊ የሥራ ውል የሌላቸው መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን በዚህም የተነሣ ዕድሜያቸው ገፍቶ አቅም ሲያጡና ከሥራ ሲወጡ ለከፋ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ቀውስ ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወቃል።



በዚህም አሽከርካሪዎች አገልግለው የመሥራት አቅማቸው ሲዳከም ጡረታ እንዲከፈላቸው በሕግ ቢቀመጥም መደበኛ የሥራ ውል ባለመኖሩ ምክንያት ሕጉ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል።



ይህ ክፍተት አሽከርካሪዎች ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደርና ልጆቻቸውን ማስተማር ባለመቻላቸው በከፍተኛ ድህነትና መቸገር ውስጥ እንዲወድቁ ዳርጓቸዋል።



ይሁን
እንጂ በኢትዮጵያ የንግድ ትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ ለዓመታት ሥር ሰዶ የቆየውን የመብት ጥሰትና የሕጋዊ የሥራ ውል እጦት በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል  የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙ በዛሬው እለት ተሰምቷል።  



ይህ ስምምነት የዘርፉን አሽከርካሪዎች የሥራ ውልና የማኅበራዊ ዋስትና መብቶች ሙሉ በሙሉ የሚያስከብር መሠረት የሚጥል መሆኑ ተገልጿል።



Advertisement
Your ad could be here — contact us

የመግባቢያ ሰነዱን በጋራ ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን እና የትራንስፖርት መገናኛ ሠራተኞች ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ሲሆኑ ስምምነቱ በየደረጃው በሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት እና የድንበር ተሻጋሪ ከባድ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች ላይ የሚታየውን ሕጋዊ የሥራ ውል አልባነት ለመቅረፍ ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት መገናኛ ሠራተኞች ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አባትሁን ታከለ ማንኛውም በንግድ ተሽከርካሪ ላይ የሚሠራ አሽከርካሪ ሕጋዊ የሥራ ውል ሊኖረው እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ሸገር ሬድዮ ዘግቧል።



ይህ ባለመኖሩ ባለንብረቶቹም ሆኑ አሽከርካሪዎቹ በእኩል ደረጃ ተጎጂዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አባትሁን ችግሩን ለመፍታት አሠሪና ሠራተኛው በየዘርፋቸው በአግባቡ እንዲደራጁ መደረጉን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘርኡ በበኩላቸው በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ግልጽና ፍትሐዊ አሠራር ለመዘርጋት በቅንጅት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።



ይህ ሥርዓት መዘርጋቱ ለአሽከርካሪው የኑሮ ዋስትና ከማረጋገጡም በላይ ለባለንብረቶችም የሥራ ሰላምና የተረጋጋ አሠራር በመፍጠር ረገድ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።



አቶ ብርሃኔ አያይዘውም የዚህን ማኅበራዊ ዋስትና ጉዳይ ዘላቂነት ለማረጋገጥ ሌሎች ባለድርሻ ተቋማትና አካላትም በሂደቱ ውስጥ እንዲሳተፉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።


የትራንስፖርትና መገናኛው ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል የማይባል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ናቸው።



አቶ ካሳሁን በሰጡት አስተያየት በዘርፉ ያሉ የአሠሪም ሆነ የሠራተኛ መብትና ጥቅሞች የማይነጣጠሉና እርስ በርስ የሚደጋገፉ መሆናቸውን አንስተዋል።

 

በአጠቃላይ የሁለቱ ፌዴሬሽኖች ይህ ስምምነት በዘርፉ ለዓመታት ሲታይ የቆየውን ሰራተኛ አለመረጋጋት፣ የደኅንነት ሥጋት እና የመብት ጥሰት በጽኑ መሠረት ላይ ለመቅረፍ ትልቅ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተስፋ ተጥሎበታል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

80 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።