Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ቢዝነስ

ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ከአለም ባንክ እና IMF የተሻለ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጹ

BS Bethelhem Solomon Sep 29, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 366 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ ከአለም ባንክ እና IMF የተሻለ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጹ

የባንኩ ቢሮ አዲስ አበባ ላይ ቢከፈት ሀገሪቷን የፋይናንሻል ሲስተም የልህቀት ማዕከል እንደሚያደርጋት እና አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን እንደሚያመጣም ተነግሯል።



ኢትዮጵያ
ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ መሪነቱን ከያዙ ሀገራት ተርታ ናት። ከግሎባል ሳውዝ ወይም ከደቡብ ደቡብ ሀገራት ጋር  ያላትን ትስስር ለማጠናከር የሚያስችላትን የብሪክስ ጥምረት በቅርቡ መቀላቀላን ተከትሎ የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ አባል ለመሆን እርምጃዋን ጀምራለች።



የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 19/2018 ዓ.ም ባካሄደው 57ኛ መደበኛ ስብሰባው የባንኩ ማቋቋሚያ ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል።  



ይህ እርምጃ እንደ ወርልድ ባንክ፣ IMF እና  IFC ያሉ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት “አንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ሊያመጣ የሚችለው ያስቀመጥናቸውን የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለሞችን ሲከተል ብቻ ነው” በሚል ከያዙት ጥብቅ እምነት የሚያላቅቅ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ኢብራሂም አብዱልአዚዚ ለገበያ ሚዲያ ተናግረዋል።
 


ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ “እኔ የመረጥኩላችሁን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ልትተገብሩ ይገባል የሚል ስትራክቸራል የሆነ ጥያቄ አያስቀምጥም” ሲሉ ባንኩ ከሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት የሚሻልበትን ምክንያት አስረድተዋል።  ባንኩ የልማት ስራዎች እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የገለጹት ባለሙያው እነዚህ የልማት ስራዎች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆኑን የሚያጣራበት መንገድ እንዳለው ተናግረዋል።   



ከተበዳሪ አንፃር ስንመለከተው የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ የብድር አማራጮች የተሻሉ እና ቀላል ናቸው ያሉት አቶ ኢብራሂም  የባንኩ መስራች ሀገራቶች የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተለያየ በመሆኑ የባንኩ አባል ሀገራት እንዲከተሉት የሚጠይቅ ኢኮኖሚያዊ  ግዴታዎች እንደሌሉት አስረድተዋል።



የተለያዩ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በርካታ የሚያስቀምጧቸው መስፈርቶች መኖራቸውን የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው በኢኮኖሚው ውስጥ መንግስት የሚኖረውን ሚና ከመወሰን ጀምሮ ሌሎች አስገዳጅ የምግብ እና የነዳጅ ድጎማዎችን እንዲነሱ ጫና እስከማሳደር ድረስ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ጠቅሰዋል።



በተጨማሪም መንግስት ወጪውን በመቀነስ የሚሰበስበውን ታክስ በተለያየ መንገድ  ማሳደግ አለበት የሚል ጥብቅ የሆነ መመሪያ እንዳላቸው ገልጸዋል። የአዲስ ልማት ባንኩ የብድር አሰጣጥ መስፈርቶችንም በተመለከተም የፋይናንስ ተቋማትን ነጻነት ከማስጠበቅ አንጻር ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት የተሻለ ቢሆንም “ሙሉ በሙሉ ንጹህ ነው” ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።   




የስርዓተ ገበያ ባለሙያ እና አማካሪ የሆኑት አቶ መርዕድ ቱሉ በበኩላቸው ባንኩ ለአባል ሃገራት ልማትን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ በማውጣት፣ የክፍያ መድረክን በማዘጋጀት እንዲሁም ንግድ እና ግብርናን በማሳለጥ በሀገራቱ መካከል ግብይቶች እንዲፋጠኑ ያደርጋል ብለዋል።   



ባለሙያው አያይዘውም ባንኩ በዶላር ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረውን የንግድ፣ የብድር እና የግብይት ልውውጥ ስርዓት ወደ የተለያዩ የአባል ሀገራት የገንዘብ ምንዛሬዎች የመለሰ መሆኑን አንስተዋል። 



በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) በ18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር “የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ አድማሱን በመላው አፍሪካ እንዲያስፋፋ የባንኩን ቀጣናዊ ቢሮ በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ኢትዮጵያ በሙሉ አቅም ዝግጁ ናት" ሲሉ መደመጣቸው አይዘነጋም።



ይህን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት አቶ መርዕድ የባንኩ ቢሮው አዲስ አበባ ላይ ቢከፈት ሀገሪቷን የፋይናንሻል ሲስተም የልህቀት ማዕከል እንደሚያደርጋት እና አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን  እንደሚያመጣ ተናግረዋል። በተጨማሪም የባንኩ ስብሰባዎች በሚካሄዱበት ወቅት ቱሪስቶችን በመሳብ ተጨማሪ አቅም እና ጥቅም ይሰጣል ያሉት ባለሙያው “በርካታ ኢኮኖሚያዊ በረከት” ይዞ እንደሚመጣ አስረድተዋል።


ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ እ.ኤ.አ በ2015 በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ደቡብ አፍሪካና ቻይና የተቋቋመ ባለብዙ ወገን ልማት ባንክ ነው።  ዋና መሥሪያ ቤቱን በሻንጋይ ቻይና ያደረገው ባንኩ በእያንዳንዱ መስራች አባል ሀገራት ውስጥ ቅርንጫፍ ያሉት ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2021 በኃላ አልጄሪያ፣ ባንግላዲሽ፣ ግብፅ፣ ተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች እና ኡዝቤክስታን በአባልነት በመቀላቀላቸው ተደራሽነቱን አስፋፍቷል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

86 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።