Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ኢትዮጲያ

በአባይ ተፋሰስ ላይ ሊሰሩ የታቀዱ ተጨማሪ ግድቦች የአለም አቀፍ ህግጋትን የጠበቁ መሆናቸው ተገለጸ

BS Bethelhem Solomon Oct 26, 2026 Updated 3h ago 1 ደቂቃ ንባብ 441 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
በአባይ ተፋሰስ ላይ ሊሰሩ የታቀዱ ተጨማሪ ግድቦች የአለም አቀፍ ህግጋትን የጠበቁ መሆናቸው ተገለጸ

ጥናቶቹ በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ባላት የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብቷ የተከበረ መሆኑም ተረጋግጧል



ከህዳሴ
ግድቡ በተጨማሪ በአባይ ተፋሰስ ላይ ሊገነቡ የታቀዱ ግድቦች የዓለም አቀፍ ህግጋትን ጠብቀው የተጠኑ መሆናቸውን በአባይ ተፉሰስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩት ተመራማሪ ዶ/ር አሰፋ ሙሉ ለገበያ ሚዲያ ተናገሩ።



ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በመጠቀም በተፋሰሱ ላይ  ተጨማሪ ግድቦችን እንደምትገነባ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሃብታሙ ኢተፋ መናገራቸው ይታወቃል።



ግብፅ  በበኩሏ ይህን በመቃወም በላይኛው የተፋሰስ ሀገሮች የሚካሄዱ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ያለ ቅድመ ማሳወቂያና ቅንጅት መቀጠል የለባቸውም የሚል አቋም በመያዝ ከተለያዩ ሃገራት መሪዎች ጋር እየተወያየች መሆኑ አይዘነጋም።



እነዚህ ተጨማሪ ግድቦች “ የኤሌክትሪክ ግድቦች  እንጂ የመስኖ ግድቦች አይደሉም” ያሉት ዶ/ር አሰፋ  ይህም ኤሌክትሪክ ከማምረት ባሻገር ምንም አይነት ውሃ የሚያስቀር ባለመሆኑ የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት  ስጋት ሊኖራቸው እንደማይገባ ተናግዋል።



እንደ ባለሙያው ገለጻ የእነዚህ ተጨማሪ ግድቦች ሁሉን አቀፍ ጥናት በኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ከ1956 እስከ 1964 ዓ.ም በአሜሪካ መሃንዲሶች አማካኝነት  የተጠና ሲሆን ዲዛይኑ ተሰርቶ የተቀመጠ ነው።



በተጨማሪም ይህ ጥናት “በጣም ወሳኝ ጥናት ነው” ያሉት ዶ/ር አሰፋ ጂኦሎጂውን ፣ ሃይድሮሎጂውን፣ የሃገር ውስጥ ኢኮኖሚውን እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ግምት ውስጥ ያስገባ  እንደሆነ ተናግረዋል።



አያይዘውም ጥናቶቹ በሳይንስ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ተናግረው ኢትዮጵያም  ባላት የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብቷ የተከበረ መሆኑን አረጋግጠዋል።



ከዚህ
ጥናት በኋላ እ.አ.አ በ1998 እስከ 99 በፈረንሳይ አማካሪ መሃንዲሶች አማካኝነት የተቀናጀ  የአባይ ተፋሰስ ማስተርፕላን መጠናቱን አስታውሰው ጥናቶቹ የኢትዮጵያ መንግስት ጨረታ አውጥቶ፣ ጥያቄ አቅርቦ የተጠኑ እና እውቅና ያላቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል።



“
እነዚህ ግድቦች ዲዛይናቸው ሁሉ በዛ በወቅቱ በነበረው ሁኔታ ተሰርቶ የተቀመጠ ነው” ያሉት ባለሙያው የወቅቱ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እያደገ ስለመጣ መሻሻሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። 



በሌላ በኩል ግብጽ የአስዋን ግድብን ስትገነባም ሆነ ከተሞችና ሜጋ ፕሮጀክቶችን ስትዘረጋ የትኛውንም የተፋሰስ ሀገር ፈቃድ አለመጠየቋን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሃብታሙ ኢተፋ ተናግረው ነበር።



ይህንን ሃሳብ ያጠናከሩት ዶ/ር አሰፋ  የግብጽ ክሶች ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው “እራሳቸውን እየከሰሱ ነው ያለው፤ መጀመሪያ አባይ ላይ ግድብ የገነቡት እነሱ ናቸው፤ ለእኛ ያሳወቁን ነገር የለም” ብለዋል። 



አያይዘውም የ1929 እና የ1959  የቅኝ ግዛት ውሎች ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸው የማታውቃቸው እና የማትቀበላቸው መሆኑን ገልጸው ምንም እንኳን ግብጽ ቀድማ አባይ ላይ ግድብ በመገንባት የተናጠል ውሳኔ ያስጀመረች ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን የሌሎችን ተጠቃሚነት እንደማትነካ አስገንዝበዋል።



በጋ ላይ ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ በግድቦቹ አማካኝነት ተጨማሪ ውኃ የሚለቀቅ በመሆኑ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ስጋትና ተጽዕኖ የሚቀንስ መሆኑንም ጠቁመዋል።በተጨማሪም ደለል ወደ የታችኛው ተፋሰስ ግድቦች እንዳይገባ በመከላከል በኩል ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አስገንዝበዋል።



በመጨረሻም እነዚህ ግድቦች ሲገነቡ የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ከፍ ከማድረግ ባለፈ ለኤክስፖርት ንግድና ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸው ህብረተሰቡም እንደ ህዳሴው ግድብ ግንባታ ሁሉ በደን ሽፋንና በተፋሰስ ጥበቃ ስራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የባለቤትነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

91 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።