የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ባከናወነው አጠቃላይ የኦዲት ምርመራ በ75 የመንግስት ተቋማት ውስጥ የተፈጸሙ የፋይናንስ ጉድፈቶች ማግኘቱን አስታወቋል።
በቢሮው የተለየው 187.7 ሚሊዮን ብር የሚገመት የፋይናንስ ግድፈት ላይ ወዲያውኑ የእርምት እርምጃዎች መወሰዳቸውን የቢሮው ሃላፊዎች ገልጸዋል።
ይህ የኦዲት ውጤት ይፋ የሆነው ከተማ አስተዳደሩ 350 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት እና የህዝብ አገልግሎት የፋይናንስ ክፍተት ባጋጠመው ወቅት ነው።
ቢሮው ያለውን ውስን የፋይናንስ አቅም በብቃት ለመምራት እና የተያዙ የልማት ግቦችን ለማሳካት የፋይናንስ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ ባለፈው ዓመት የነበረውን የኦዲት እቅድ አፈጻጸም በ171 በመቶ በማሳደግ የቁጥጥር ስራውን ወደ 3,242 ተቋማት ማስፋት ችሏል።
የኦዲት ሪፖርቶች ጥራትም ወደ 85 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉ የቢሮውን የክትትል አቅም ማደግ የሚያሳይ ነው የተባለ ሲሆን ይህ የላቀ አፈጻጸም የአዲስ አበባን የፋይናንስ አስተዳደር ከአፍሪካ ቀዳሚ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያስቻለ ነው ተብሏል።
በአፍሪካ ከተሞች መካከል በተደረገ የፋይናንስ አስተዳደር ግምገማ አዲስ አበባ ከአህጉሪቱ ታላላቅ ከተሞች መካከል ቀዳሚ ሆና መመረጧን በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደ የክልላዊ የልምድ ልውውጥ አውደ ጥናት ላይ ይፋ እንደተደረገው አዲስ አበባ በገቢ አሰባሰብ እና በፋይናንስ ሀብት ምደባን ጨምሮ በስድስት ዋና ዋና መመዘኛዎች ውስጥ በአምስቱ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ከናይሮቢ፣ ዳሬሰላም፣ ሉሳካ፣ ኪጋሊ እና ያውንዳ መሪ መሆን ችላለች።
የፋይናንስ ቁጥጥር ስራውን ዘመናዊ እና ውጤታማ ለማድረግ ቢሮው በሰው ኃይል እና በአሰራር ሂደት ላይ ትኩረት ማድረጉን አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት የውስጥ ኦዲት ስራውን የሚመሩት 80 በመቶ የሚሆኑት ባለሙያዎች ረጅም የሥራ ልምድ ያላቸው መሆናቸው ቢሮው ተግዳሮቶችን አስቀድሞ በመለየት ለመፍታት ለሚከተለው ስልት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተገልጿል።
የቢሮው ሃላፊዎች እንደገለጹት የተጠናከረ የፋይናንስ ቁጥጥርና የኦዲት አፈጻጸም ለልማት አጋሮች እና ለውጭ አበዳሪ ተቋማት ያለውን እምነት ለማስቀጠል ወሳኝ ነው።
ይህም ከተማዋ በመሠረተ ልማት ግንባታ እና በህዝብ አገልግሎት መስጫ ዘርፎች የገጠማትን የ350 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት በሚደረገው ጥረት የገንዘብ ምንጮችን ለመሳብ እና በከተማዋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ መተማመንን ለመገንባት የሚያግዝ ስትራቴጂክ እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህ የሪፎርም ጉዞ አዲስ አበባ የፋይናንስ ግልጽነትን በማረጋገጥ የከተማ ልማት ዘላቂነትን ለመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየወሰደች ያለችውን የለውጥ እርምጃ ያሳያል።