Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2018 በጀት ዓመት 9.1 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

BS Bethelhem Solomon Jul 29, 2026 Updated 3h ago 1 ደቂቃ ንባብ 87 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2018 በጀት ዓመት 9.1 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ 20.7 ሚሊየን ደንበኞችን ማጓጓዙንም ገልጿል።


የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርቱን ዛሬ ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም ይፋ አደርጓል። 

በዚህም አየር መንገዱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 9.1 ቢሊየን ዶላር (ከ1.4 ትሪሊየን ብር በላይ) ገቢ ማግኘቱን የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በመግለጫው አስታውቀዋል።

አቶ መስፍን በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ20 በመቶ ዕድገት ያሳየ ቢሆንም፤ከታቀደው ዕቅድ አንፃር ግን በተወሰነ መልኩ ቅናሽ አሳይቷል።

ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል በመካከለኛው ምስራቅና በገልፍ ሀገራት የተፈጠረው የፀጥታ ችግር፣ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ፣ በትላልቅ አውሮፕላኖች ላይ አጋጥሞ የነበረው እጥረት እንዲሁም በአንዳንድ ሀገራት የተጣሉ አዳዲስ የጉዞ ማዕቀቦች ተጠቅሰዋል። 

በበጀት ዓመቱ አየር መንገዱ 20.7 ሚሊየን መንገደኞችን ያጓጓዘ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ10 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። እንዲሁም 897 ሺህ ቶን የካርጎ ጭነት በማጓጓዝ ከቀድሞው ዓመት የ16 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል።

በተጨማሪም 4 አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በመጨመር አጠቃላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን 150 ያደረሰ ሲሆን የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችንም ከ22 ወደ 25 ማድረስ ችሏል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

በዚሁ ዓመት 9 አዳዲስ አውሮፕላኖች በግዢና በኪራይ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን አየር መንገዱ ከአውሮፕላን ማረፊያ እና ከበረራ አገልግሎት ባሻገር፤ ለአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ አካላትን በማምረት ለ68 አውሮፕላኖች የሚሆኑ ክፍሎችን አምርቶ በማስረከብ 6.8 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ገቢ አግኝቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በድጋሚ በማሻቀቡ እና በገልፍ ሀገራት ቀውስ ሳቢያ የነዳጅ ማጓጓዝ ሂደቱ ፈተና በመገጥሙ፤ የአየር መንገዱ ዓመታዊ የሥራ ወጪ በ25 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል። 

እንዲሁም በዚሁ ቀውስ ምክንያት ወደ ቀጠናው ይደረጉ የነበሩ 10 የሚሆኑ በረራዎች መቋረጣቸውና በአፍሪካ እና በሰሜን አሜሪካ መካከል የነበረው ጉዞ መቀነሱ ለሥራው ፈተና ፈጥረው እንደነበር ተነግሯል።


አየር መንገዱ በቀጣዩ በጀት ዓመት የገቢ መጠኑን ወደ 10 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ አቅዶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በሌላ በኩል የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መንደርደሪያን የማሻሻል እንዲሁም የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የማዘመን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል። 


ለታቀደው የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ግንባታ በቦታው የነበሩ አርሶ አደሮችን የማስፈር ሥራ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን ለአጠቃላይ ግንባታው የሚሆን ብድር የማፈላለግ ሥራ በመሰራት ላይ ይገኛል ተብሏል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

54 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።