በአዲስ አበባ ከተማ በትራፊክ ፖሊሶች እና በአሽከርካሪዎች መካከል የሚታዩ የሥነ-ምግባር ችግሮችን ለመቅረፍ እና የተጠያቂነት አሠራርን በቴክኖሎጂ ለማጠናከር የትራፊክ ፖሊሶች የሰውነት ካሜራዎችን እና የተሽከርካሪ ካሜራዎችን ሊታጠቁ መሆኑ ተገለጸ።
በተያዘው ዓመት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የትራፊክ ሕግ ጥሰቶች መመዝገባቸውን በአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ዋና መምሪያ የግንዛቤ ማስጨበጥ ምክትል መምሪያ ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር የሆኑት ሰለሞን አዳነ አብራርተዋል።
ተቋሙ በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት የሚታዩ ክፍተቶችን በቴክኖሎጂ ታግዞ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው የትራፊክ ፖሊሶች የሚታጠቋቸው የሰውነት ካሜራዎች እና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚገጠሙ ካሜራዎች ከአሽከርካሪዎች ጋር የሚደረገውን ግንኙነት ከማዕከል በቀጥታ ለመከታተልና የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።
ይህንኑ አሠራር አስመልክቶ ዋና ኢንስፔክተሩ "በተለይ እንግዲህ እንደነዚህ አይነት ችግሮችንም ለመቅረፍ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመን እየሰራን ያለንባቸው ሁኔታዎች አሉ ማለት ነው። የተሽከርካሪ ካሜራዎችን የትራፊክ ፖሊስ ቦዲ ካሜራዎችን ተጠቅመን ከአሽከርካሪዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመከታተል ከማዕከል የስራ መመሪያዎችን የማስተካከያ ሂደቶችን ወይም ሁነቶችን እየተከታተልን እያረምን የሚሄድባቸው ሁኔታዎች አሉ" ብለዋል።
ከትራፊክ ቅጣቶች ጋር ተያይዞ ቅጣቱ "ለገቢ መሰብሰቢያ ታቅዶ የሚሰራ ነው" በሚል በአሽከርካሪዎች ዘንድ ለሚነሱ ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት ዋና ኢንስፔክተሩ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ እንደ ሌሎቹ የንግድ ተቋማት በጀት ተይዞለት ገቢ ለመሰብሰብ የሚሰራ ሳይሆን ዋና ዓላማው ውድ የሆኑ የዜጎችን ሕይወት ከሞት እና ከአካል ጉዳት መታደግ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በከተማዋ ከ900 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ከተመዘገቡት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሕግ ጥሰቶች መካከል ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት የቀይ መብራት ጥሶ ማለፍ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አሽከርካሪዎች ሕግ ሲተላለፉ አስተምሩን እንጂ አትቅጡን እያሉ ከሚያነሱት ቅሬታዎች ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የሚያሳዩት ከግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ጎን ለጎን ጠንካራ የሕግ አፈጻጸም ቁጥጥር ሲኖር ብቻ አደጋን መቀነስ እንደሚቻል ነው ብለዋል።
የቁጥጥር እና የቅጣት አፈጻጸሙ መጠናከሩ አደጋዎችን በመቀነስ ረገድ አዎንታዊ ውጤት እያሳየ ይገኛል ያሉት ዋና ኢንስፔክተሩ በ2017 ዓ.ም 411 የነበረው የሞት አደጋ በ2018 ዓ.ም ወደ 382፤ የከባድ አደጋዎች ቁጥር ደግሞ ከ1,985 ወደ 1,865 ዝቅ በማለት የ120 አደጋዎች ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁመዋል።
በአንጻሩ ቀላል አደጋዎች ከ115 ወደ 735፣ የንብረት ጉዳቶች ደግሞ ከ34,084 ወደ 34,702 ከፍ ማለታቸው ተመላክቷል።በተጨማሪም አሽከርካሪዎች ነባር ሕጎችን እና የመንገድ ላይ ምልክቶችን በትክክል የማወቅ ሕጋዊ ግዴታ እንዳለባቸው ተገልጿል።