ኢንስታግራም እና ፌስቡክን የሚያስተዳድረው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሜታ ታዳጊዎችን ለአደጋ እና ለማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ የሚያጋልጡ አሠራሮችን ተጠቅሟል በሚል ከአሜሪካ 30 ግዛቶች የቀረበበት ክስ በፍርድ ቤት ሊታይ መሆኑ ተገልጿል።
ክሱ ከተረጋገጠ በኢንስታግራም እና ፌስቡክ የሚገኙ እንደ 'ላይክ'፣ ኢንፋይናይት ስክሮል፣ አውቶፕሌይ እና ተደጋጋሚ ኖቲፊኬሽን ያሉ ባህሪያት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊደረግ ይችላል ተብሏል።
ካሊፎርኒያ እና ኒውዮርክን ጨምሮ 30ዎቹ የአሜሪካ ግዛቶች ሜታ ታዳጊዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ላይ ረዥም ሰዓት እንዲቆዩና ደጋግመው ወደ መተግበሪያዎቹ እንዲመለሱ የሚያደርጉ አሠራሮችን በመጠቀም የታዳጊዎችን ደኅንነት አልጠበቀም ሲሉ ከሰዋል።
በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ አሠራሮች ተጠቃሚዎች አንድ ይዘት ካዩ በኋላ ተመሳሳይ ወይም ሌላ አሳታፊ ይዘት ወዲያውኑ እንዲያዩ በማድረግ ተጠቃሚውን በመተግበሪያው ላይ እንዲቆይ የሚያበረታቱ ናቸው የሚል ክርክር ቀርቦበታል።
ከክሱ ዋና ነጥቦች አንዱ 'ላይክ' ሲሆን በተለይ ታዳጊዎች የሚያገኙትን የ'ላይክ' ብዛት ከሌሎች ጋር በማወዳደር ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ ከማኅበራዊ ሚዲያ ምላሽ ጋር እንዲቆራኝ ሊያደርግ ይችላል ተብሏል። ይህም የብቸኝነት፣ የመገለል ስሜት፣ የሰውነት ገጽታን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት እና ሌሎች አሉታዊ ስሜቶችን ሊያባብስ እንደሚችል ተጠቁሟል።
የአሜሪካ ግዛቶቹ ፍርድ ቤት ሜታ በታዳጊዎች አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ለውጦችን እንዲያደርግ እንዲያዝ ሲጠይቁ ከእነዚህም ታዳጊዎች የሚጠቀሙበትን አካውንት ቤተሰቦች እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል ሥርዓት ማጠናከር እና የማያቋርጥ ኢንፋይናይት ስክሮል አሠራርን መገደብ ተካቷል።
በተጨማሪም አንድን መረጃ አስከትሎ ሌላ ዶፓሚን ሆርሞንን የሚያነቃቃ መረጃ አለመስጠት፣ የሰዎችን ገጽታ መለወጥ የሚችለውን ፊልተር ማቆም፣ የ‘ላይክ’ ቁጥርን እንዳይታይ ማድረግ ብሎም ቪድዮዎች በራሳቸው እንዲጫወቱ የሚያደርገውን አውቶፕሌይ ማቆም የሚለውም ይገኝበታል።
እንዲሁም ተጠቃሚዎች ብዙ አካውንቶችን እንዳይከፍቱ መገደብ እና ታዳጊዎችን በተደጋጋሚ ኖቲፊኬሽን ወደ መተግበሪያዎቹ እንዲመለሱ የሚያደርጉ አሠራሮችን መቀነስ እንደሚኖርበትም ተጠይቋል።
ሆኖም ሜታ ክሱን ያልተቀበለ ሲሆን ኩባንያው ታዳጊዎችን ለመደገፍ የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጾ፣ በፍርድ ቤት የቀረቡትን ክሶች በማስረጃ እንደሚቃወም አስታውቋል።
ሜታ በተጠየቀው መሠረት አሠራሩን እንዲቀይር ከተወሰነ ኢንስታግራምና ፌስቡክ ከሚታወቁበት በእጅጉ የተለዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል። ኩባንያው በቅርቡ ኒው ሜክሲኮ ውስጥ በተካሄደ ሌላ የፍርድ ሂደት 942 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል።