Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

አዲስ አበባ ከፍተኛ በካይ ተሽከርካሪዎች የማይገቡባቸው ልዩ ቀጠናዎች ሊኖሯት ነው

BS Bethelhem Solomon Sep 14, 2026 2 ደቂቃ ንባብ 33 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
አዲስ አበባ ከፍተኛ በካይ ተሽከርካሪዎች የማይገቡባቸው ልዩ ቀጠናዎች ሊኖሯት ነው

ከዚህ በተቃራኒው እነዚህን አካባቢዎች ንጹህ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጮች ማለትም እንደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያሉ ብቻ እንዲጠቀሙባቸው የማድረግ ስራ ይሰራል ተብሏል።


አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተባባሰ የመጣውን የአየር ብክለት ለመቀነስ እና የህዝብ ጤናን መጠበቅ ከፍተኛ በካይ የሆኑ ተሽከርካሪዎች የማይገቡባቸው ልዩ ቀጠናዎች ለመከለል እና የቦሎ አሰጣጥ ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አጠቃላይ እቅድ ማዘጋጀቱ ተሰማ።


ከአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በሚተገበረው በዚህ አዲስ አሰራር መሰረት የካርቦን ልቀታቸው ከፍ ያለ እና አካባቢን በከፍተኛ ሁኔታ የሚበክሉ ተሽከርካሪዎች ወደ ተመረጡ እና ተከለሉ ልዩ ቀጠናዎች እንዳይገቡ ክልከላ ይደረጋል።


ከዚህ
በተቃራኒው እነዚህን አካባቢዎች ንጹህ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጮች ማለትም እንደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያሉ ብቻ እንዲጠቀሙባቸው የማድረግ ስራ እንደሚዘረጋ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።

ይህ እቅድ በከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴና በአየር ጥራት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለተግባራዊነቱም ከወዲሁ የተቀናጁ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ ተብሏል


 የከተማዋን አየር ከዕለት ወደ ዕለት እየበከሉ የሚገኙ ተሽከርካሪዎችን ምንጭ ለማድረቅም በሁለተኛው ምዕራፍ ጥብቅ የቁጥጥር ስልቶች የተነደፉ ሲሆን በተለይም ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ አድርገው የሚያገኙትን የቦሎ ምስክር ወረቀት በተመለከተ ጠንካራ እና የማይበገር ቁጥጥር እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us


የቦሎ እድሳት በሚደረግበት ወቅት ተሽከርካሪዎች የተጣለባቸውን የጭስ ልቀት ስታንዳርድ ማሟላታቸው በምርመራ ተቋማት በድጋሚ በጥብቅ የሚረጋገጥ ይሆናል። በዚህ ምርመራ ወቅት መስፈርቱን የማያሟሉ ተሽከርካሪዎች አስፈላጊውን የሞተር እና የቴክኒክ ማስተካከያ ሳያደርጉ ቦሎ በፍጹም እንደማይታደስላቸው ተገልጿል።

ይህንን አሰራር በየደረጃው ለማስፈጸም የትራንስፖርት ቢሮው እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን  በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይም በድንገተኛ ፍተሻዎች አማካኝነት የልቀት መጠናቸው ከሚፈቀደው ስታንዳርድ በላይ ሆኖ የተገኙ ተሽከርካሪዎች ከህግ አግባብ ውጭ ወዲያውኑ ከአገልግሎት እንዲወገዱ ይደረጋል ተብሏል።

በተጨማሪም አዲሱን አሰራር ወደ መሬት አውርዶ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ለማስገባት ጠንካራ ክትትልና የቁጥጥር መረብ እንደሚዘረጋ ተሰምቷል።


የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የትራንስፖርት ቢሮ ይህንን ሀገራዊና ህዝባዊ አላማ ስኬታማ ለማድረግ የተሽከርካሪ ባለቤቶችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ባለቤቶቹ ተሽከርካሪዎቻቸውን በየጊዜው በመጠገን እና የቴክኒክ ብቃታቸውን በማረጋገጥ የአየር ብክለትን በመከላከል ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስቧል።

ከተሽከርካሪዎች በሚወጣ በካይ ጋዝ የሚደርስ የአየር ብክለትን ለመከላከል በኢትዮጵያ የሚዘወሩ ተሽከርካሪዎች ብክለት መጠን የሚቆጣጠር አስገዳጅ መመሪያ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ መነገሩ የሚታወስ ነው።


በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ የተሰናዳው መመሪያ በተሽከርካሪዎች የበካይ ጋዝ ልቀት ምክንያት የሚደርስ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ተሽከርካሪዎች ይህንን የሚቆጣጠር ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

81 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።