Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

በመዲናዋ የቀበሌ ቤቶችን በሕንጻዎች የመተካት አዲስ ስትራቴጂ ይፋ ተደረገ

BS Bethelhem Solomon Jun 18, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 168 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
በመዲናዋ የቀበሌ ቤቶችን በሕንጻዎች የመተካት አዲስ ስትራቴጂ ይፋ ተደረገ

መንግስት ለአዳዲስ ቦታዎች ፍለጋ ከፍተኛ የካሳ ወጪ እየከፈለ ከመገንባት ይልቅ ያሉትን ሰፋፊ የቀበሌ ቦታዎች በዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መተካት ይገባል ተብሏል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን የመሬት አጠቃቀም በዘላቂነት ለማዘመን ሰፋፊ ግቢ ያላቸውና ስልታዊ ቦታ ላይ የሚገኙ የቀበሌ ቤቶችን በባለ አራት፣ አምስት እና ከዚያ በላይ ወለል ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመተካት ስትራቴጂ ይፋ ድርጓል።


የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከመላው የከተማው አመራር ጋር ባደረጉት የምክክር መድረክ ይህ አዲስ አሰራር 90 ቀናት የክረምት እቅድ ዋነኛ አካል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ እንደተገለጸው የቆየው የቀበሌ ቤቶችን በቆርቆሮና በቀለም በመጠገን የቁጥር ማብዛት አካሄድ በይፋ ይቆማል።


ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳስገነዘቡት የከተማዋን መሬት በአግባቡ ለመጠቀም ሰፋፊ ግቢ ያላቸውና ስልታዊ ቦታ ላይ የሚገኙ የመንግስት ይዞታዎች ተለይተው በምትኩ አነስተኛ ቦታ ላይ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል ሊስተናገድባቸው የሚችል ባለከፍታ ሕንጻዎች ይገነባሉ።


መንግስት አዳዲስ ቦታዎችን ፍለጋ ከፍተኛ የካሳ ወጪ እየከፈለ ከመገንባት ይልቅ ያሉትን ሰፋፊ የቀበሌ ቦታዎች በዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መተካት ይገባል ያሉት ከንቲባዋ የመንግስትን ተጨማሪ ወጪ የሚቀንስና መሬትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል አማራጭ ነው ብለዋል።


ይህ ስትራቴጂ ነባር ነዋሪዎችን በማፈናቀል ሳይሆን በቦታው ላይ ዘመናዊ ባለከፍታ ሕንጻዎችን በመገንባት ነባር ነዋሪዎችን ጨምሮ ተጨማሪ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው።

መንግስት የደሃውን ቤት ጓዳ አይቶ የሚያጎርስ እንጂ ነዋሪዎችን በዘፈቀደ የሚያፈናቅል አይደለም ያሉት ከንቲባዋ የቀበሌ ቤቶች ባሉበት ቦታ አዳዲስ ቤቶች ሲገነቡ ነባር ነዋሪዎች ቅድሚያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እና ይህ አሰራር 90 ቀናት እቅድ ውስጥ ተካቶ በልዩ ንቅናቄ እንደሚፈጸም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።


በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ሰፋፊ ግቢ ያላቸውን ቦታዎች ለጥገና ሳይሆን ዘላቂና የማይፈርሱ ቤቶችን ለመገንባት እንዲውሉ መመሪያ አስተላልፏል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ከቤት ልማቱ ጋር በተያያዘ የቀበሌ ቤቶችን በህገ-ወጥ መንገድ የያዙ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ በጥንቃቄ እንደሚመራ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።


በዚህ ረገድ ህገ-ወጥ የተባሉ ይዞታዎችን ለመለየት የሚያስችል መመሪያ እንደሚወርድ የተገለጸ ሲሆን አመራሩ በስሜታዊነት ወይም ያለ በቂ መረጃ ዜጎችን ከቤት ማስወጣት እንደሌለበት እና አሰራሩ በግልጽነትና በፍትሃዊነት እንዲመራ ተጠቁሟል።  


እንዲሁም አመራሮች የቀበሌ ቤቶችን መረጃ በካርታና በቦታ በመለየት ለከተማ አስተዳደሩ ማቅረብ እንዳለባቸው ታዟል።

ከቤት ልማቱ በተጨማሪ ከተማዋ በከፍተኛ ወጪ እያካሄደችው ካለው የ "ትራንስፎርሜሽን" ስራ በኋላ በክረምት ወቅት የሚከሰት የጎርፍ አደጋ የከተማዋን ገጽታ እንዲያበላሽ እንደማይፈቀድ ከንቲባዋ አስገንዝበዋል።

በክረምት ወራት 175 ሺህ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በበጎ ፈቃድ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል የተባለም ሲሆን የገቢ መሰረትን ለማስፋትና የግብር አሰባሰብ ስርአቱን ለማዘመን፣ በርካታ የመሬትና የንግድ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል ማዕከል እንዲገቡ እንደሚደረግም ተገልጿል።

በተጨማሪም የታቀዱት ስራዎች ተፈጻሚነት በየደረጃው በሚገኘው የክፍለ ከተማ አመራር ትከሻ ላይ እንደሚወድቅና አፈጻጸሙም በየጊዜው በዝርዝር እንደሚገመገም በመድረኩ ተገልጿል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

11 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።