የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2017 በጀት ዓመት የሒሳብ ምርመራ ሪፖርት የመንግሥት ተቋማት የሒሳብ አያያዝ ሥርዓትን በመጣስ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ማባከናቸውን አጋለጠ።
በ65 ገጾች በተሰናዳው በዚህ ሰነድ በተለያዩ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ግልጽነት የጎደለው አሠራር እና ሕገ-ወጥ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች መስፈናቸው በግልጽ ተመላክቷል።
እንደ ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ግኝት መሥሪያ ቤቶቹ የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳያቀርቡ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ያለምንም ማስረጃ የተፈፀመ 35.8 ሚሊዮን ብር፣ ደንብና መመሪያን ያልተከተለ 57.8 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በብልጫና በድጋሚ ክፍያ መልክ 280.6 ሚሊዮን ብር ያለ አግባብ ወጪ መደረጉ ተረጋግጧል።
ለዚህ ብክነት ተጠያቂ ተብለው ከተጠቀሱት መካከል ጤና ሚኒስቴር 231.1 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን 23 ሚሊዮን ብር እና የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በግንባር ቀደምነት ይገኙበታል።
በሌላ በኩል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ አያያዝ መመሪያን በመጣስ በ138 መሥሪያ ቤቶች እና በ18 ቅርንጫፎች በወቅቱ ያልተወራረደ 16.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩ በሪፖርቱ ተጋልጧል።
በሕግ አግባብ ለሥራ ማስኬጃ ወይም ለውሎ አበል የተሰጠ ቅድሚያ ክፍያ በሰባት ቀናት ውስጥ መወራረድ እንዳለበት ቢደነግግም ተቋማቱ ይህን ደንብ በመጣሳቸው ከፍተኛ ገንዘብ ለዓመታት ተይዞ እንዲቆይ ሆኗል።
ከዚህ ተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ 4.6 ቢሊዮን ብር ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት፣ 6.6 ቢሊዮን ብር ከአንድ እስከ አምስት ዓመት፣ እና 4.8 ቢሊዮን ብር ከአምስት እስከ አስር ዓመት በላይ የቆዩ ናቸው። በዚህም የጤና ሚኒስቴር 3.4 ቢሊዮን ብር በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በ2016 እና ከዚያ በፊት ባሉት በጀት ዓመታትም በተደረጉ ኦዲቶች ከህግ ውጭ የተፈጸሙ ክፍያዎች ተመላሽ እንዲደረጉ ቢታዘዝም ውጤታማነቱ ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
በወቅቱ ከተጠየቀው 21.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ ተመላሽ ሊደረግ የቻለው 31 በመቶው ወይም 6.6 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው። ወደ 15 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ እስካሁን ለመንግሥት ካዝና አልተመለሰም።
በተመሳሳይም ከ23 ሺህ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ሙሉ በሙሉ ተመላሽ ሳይደረግ መቅረቱ የሪፖርቱ ሌላኛው አሳሳቢ ግኝት ነው።
የኦዲት ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በተለያዩ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የሒሳብ መዝረክረክ የሚታይ ሲሆን አንዳንድ ተቋማት በተሰጠው አስተያየት መሠረት የወሰዱትን የማስተካከያ እርምጃ ተከትሎ የገንዘብ ተመላሽ ማድረግ ችለዋል።
ለዚህም በምሳሌነት የቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ 3.2 ቢሊዮን ብር፣ የኮምቦልቻ ጉምሩክ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ፣ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 120.7 ሚሊዮን ብር መመለሳቸው በሪፖርቱ እንደ መልካም ተሞክሮ ተነስቷል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት በግዴለሽነት መባከኑን በማውገዝ፣ እስካሁን ተመላሽ ያልተደረገው 15 ቢሊዮን ብር በአስቸኳይ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
መሥሪያ ቤቶቹ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያልተወራረደ ሂሳብ በአስቸኳይ እንዲወራረድ እና ሊሰበሰብ የማይችለው ደግሞ ከመዝገብ እንዲሰረዝ ኦዲተሩ አሳስቧል።