Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

የባንክ ሂሳብ ቁጥርን መሸጥና ማከራየት ለከባድ የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚዳርግ ተገለጸ

BS Bethelhem Solomon Jul 3, 2026 Updated 13h ago 2 ደቂቃ ንባብ 630 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
የባንክ ሂሳብ ቁጥርን መሸጥና ማከራየት ለከባድ የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚዳርግ ተገለጸ

ስልክ ቢጠፋ ወይም ቢሰረቅ እንኳን የባንክ ባለቤቱ ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረገ ከተጠያቂነት የማያመልጥ በመሆኑ ስልክ ሲሰረቅ ወዲያውኑ ለባንክ በማሳወቅ ሂሳቡን መዝጋት ወይም ሲም ካርድን ማገድ እንደሚያስፈልግ ተመክሯል።

የባንክ ሂሳብ ቁጥርን ለሶስተኛ ወገን በመሸጥ፣ በማከራየት ወይም ለተለያዩ ህገ-ወጥ ግብይቶች እንዲውል በመፍቀድ የሚፈጸም የወንጀል ድርጊት በሀገራችን በስጋት ደረጃ መበራከቱን  በፍትህ ሚኒስቴርጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ አስታውቋል


በባንክ አሰራር "ሂሳብ መሸጥ ወይም ማከራየት" የሚባል ህጋዊ አሰራር በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ አቃቤ ህጉ ገልጿል።


ይሁን እንጂ አጭበርባሪዎች ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወገኖችን ወይም ወዳጅ ዘመዶችን በመጠቀም በሌሎች ስም በተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች አማካኝነት በወንጀል የተገኘ ህገ-ወጥ ገንዘብን ለማዘዋወር እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ በውስጥ ምርመራ ተረጋግጧል።

አጭበርባሪዎቹ የአካውንት ባለቤቶችን አነስተኛ የገንዘብ መጠን በመክፈል፣ በማማለል፣የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎችን በራሳቸው ስልክ ላይ በመጫንና የባንክ ሂሳብ ቁጥሩን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴያቸውን እንደሚያከናውኑም ተገልጿል።


ወንጀለኞቹ በዋናነት የሚያተኩሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳቦች ላይ ሲሆን ይህ የሆነበት ምክንያት ባንኩ በስፋት ተደራሽ በመሆኑ ነው


በዚህም የባንክ ሂሳቦቹን 1,550 እስከ 5,000 ብር በሚደርስ ክፍያ ከገዙ በኋላ የይለፍ ቃሉን ጨምሮ ሙሉ መረጃዎችን በመቆጣጠር በወንጀል የተገኘን ገንዘብ በሌሎች ስም በማዘዋወር የራሳቸውን ማንነት ከህግ አካላት ለመደበቅ እንደሚሞክሩ ተገልጿል።

በተጨማሪም አጭበርባሪዎቹ "ከቤተሰብ ወይም ከጓደኛ የመጣ ገንዘብ ነው፤ በአንተ አካውንት ገቢ ይደረግና ለምነግርህ ሰው አስተላልፍ የተወሰነውን ደግሞ አንተ ያዘው" በሚሉ አሳሳች ሰበቦች ንጹሃን ዜጎችን ሳያውቁት ወደ ከባድ የወንጀል ድርጊት እንዲገቡ እያደረጉ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።


አንድ ሰው በማወቅም ይሁን በግዴለሽነት የባንክ ሂሳቡን ለሌላ አካል አሳልፎ ሰጥቶ በሂሳቡ ላይ በወንጀል የተገኘ ገንዘብ ከተዘዋወረ፤ በህግ ፊት ቀዳሚ ተጠያቂ የሚሆነው አካውንቱ በስሙ የተከፈተው ባለቤት መሆኑን በፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር / እጣወርቅ ተስፋዬ ገልጸዋል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

በስማችን በተመዘገበ አካውንት የሚገባ ማንኛውም ግብይት ተጠያቂነትን ያስከትላል ያሉም ሲሆን በቸልተኝነት እንኳን ቢሆን ለወንጀል መፈጸሚያ አካውንትን አሳልፎ መስጠት የድርጊት ተሳትፎን እንደሚያሳይ አብራርተዋል።

"ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም" ያሉት ምክትል ዳይሬክተሯ ሰዎች ለጥቂት ብር ሲሉ እስከ 25 ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል ውስጥ እየተሳተፉ መሆኑን አጥብቀው አስጠንቅቀዋል።


ስልክ ቢጠፋ ወይም ቢሰረቅ እንኳን የባንክ ባለቤቱ ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረገ ከተጠያቂነት የማያመልጥ በመሆኑ ስልክ ሲሰረቅ ወዲያውኑ ለባንክ በማሳወቅ ሂሳቡን መዝጋት ወይም ወደ ሌላ ቁጥር መቀየር እንዲሁም ሲም ካርድን ማገድ እንደሚያስፈልግ ተመክሯል።

ይህ የገንዘብ ማዘዋወር ወንጀል ለሀገር ኢኮኖሚና ለዜጎች ደህንነት ትልቅ ስጋት መሆኑን የጠቆሙት / እጣወርቅ ህብረተሰቡ የባንክ ሂሳቡን ለሌሎች በማሳለፍ ለከባድ የወንጀል ተጠያቂነት እንዳይዳረግ አሳስበዋል።


በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ እና ሌሎች የመገናኛ መንገዶችን በመጠቀም የሚቀርቡ አጠራጣሪ የገንዘብ ልውውጥ ጥያቄዎችን በመከላከል ማንኛውም ግለሰብ የራሱን የባንክ ሂሳብ በራሱ ቁጥጥር ስር ብቻ እንዲያደርግ በጥብቅ መክረዋል።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

52 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።