በአዲስ አበባ ከተማ በየካ ክፍለ ከተማ ሾላ ገበያ አካባቢ በግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በህገ-ወጥ መልኩ ተከማችተው የነበሩ ግምታዊ ዋጋቸው 8 ሚሊዮን 664 ሺህ 495 ብር የሚያወጡ የተበላሹና አገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ የኩላሊት እጥበት ኬሚካሎችና የህክምና መሣሪያዎች መወገዳቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ እና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
እርምጃውን የወሰደው የባለሥልጣኑ የየካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሲሆን የተገኙት ኬሚካሎች ለኩላሊት እጥበት ህክምና የሚያገለግሉ (Hemodialysis A) እና (Hemodialysis B) መሆናቸውን ገልጿል።
በመጋዘኑ ውስጥ ከተደረገው ማጣራት ባለፈ ሕገ-ወጥ ድርጊቱን የፈጸመውና ከስታንዳርድ ውጪ የሆነው ክሊኒክም ተጨማሪ አገልግሎት እንዳይሰጥ መታገዱ ተረጋግጧል።
በባለሥልጣኑ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት አቶ ሲሳይ ሁንዴ እንደገለጹት የተከማቸው የህክምና መገልገያና ኬሚካል "ከኩላሊት እጥበት ክሊኒክ ስር የሚገኝ ስቶር ነው" የሚል ሽፋን የተሰጠው ቢሆንም በየካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እውቅናና የብቃት ማረጋገጫ የሌለው ሕገ-ወጥ ክምችት መሆኑ ተረጋግጧል።
በመጋዘኑ ውስጥ በድምሩ 34 ዓይነት የህክምና መሣሪያዎችና የኩላሊት እጥበት ኬሚካሎች የተገኙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 14 ዓይነት ምርቶች ሙሉ በሙሉ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ናቸው።
በተጨማሪም 2 ዓይነት ምርቶች የጊዜ ገደባቸው ያላለፈ ቢሆንም፣ በተገቢው ሁኔታ ባለመከማቸታቸው ለአገልግሎት ብቁ እንዳልሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 18 ዓይነት ምርቶች ለአገልግሎት የሚያበቃቸው ሁኔታ ላይ በመገኘታቸው ሳይወገዱ ቀርተዋል።
በሂደቱ በተደረገው ማጣራትም አጠቃላይ የተወገዱት ምርቶች ግምታዊ ዋጋ 8 ሚሊዮን 664 ሺህ 495 ብር ሲደርስ ከዚህ ውስጥ ጊዜያቸው ያለፈባቸው 14 ዓይነት የኩላሊት እጥበት ኬሚካሎች 8 ሚሊዮን 615 ሺህ 495 ብር የሚገመቱ መሆናቸው ተገልጿል።
እንዲሁም በአቀማመጥ ጉድለት ምክንያት ለአገልግሎት የማይውሉት ሁለት ዓይነት ኬሚካሎች 49 ሺህ ብር ግምታዊ ዋጋ እንዳላቸው ተመላክቷል።
እነዚህ የተወገዱ ምርቶች በአለርት ኮምፕረንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሚገኝ የህክምና ኬሚካሎችና መድኃኒት ማቃጠያ ተቃጥለው እንዲወገዱ ተደርለዋል።
በምርቶቹ ላይ በተደረገው የጊዜ ገደብ ምርመራ የተገኙት ዕቃዎች ከ2021 እስከ 2026 ያሉ ቀናትን የሚያሳዩና ጊዜያቸው ካለፈ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ መሆናቸው ተመላክቷል።
የየካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋንታሁን ታደሰ ባለሥልጣኑ ባደረገው ቅኝትና ክትትል ኃላፊነት የጎደለው የጤና ግብዓት ክምችት ሊያስከትለው ከሚችል የከፋ የጤና ስጋት ሕብረተሰቡን ቀድሞ መከላከል መቻሉን ገልጸዋል።
የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ሙሉእመቤት ታደሰ በበኩላቸው ተቋሙ ጉዳዩን በጥብቅ እንደሚከታተለው ገልጸው በጤና ተቋማት እና በመድኃኒት ማከማቻዎች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
አያይዘውም የጤና ተቋማት ለሚሰሯቸው ስራዎች ህጋዊነትን እና ስስታንዳርድን አስጠብቀው ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ወስደው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።