Gebeya Media 💧
Loading…
Gebeya Media
Advertisement
ዜና

አሽከርካሪዎች የቅጣትና የወለድ ውዝፍ አሁንም እንግልት እየፈጠረ ነው ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ

BS Bethelhem Solomon Aug 22, 2026 Updated 3h ago 2 ደቂቃ ንባብ 432 እይታዎች 0 አስተያየቶች
አጋራ፦
አሽከርካሪዎች የቅጣትና የወለድ ውዝፍ አሁንም እንግልት እየፈጠረ ነው ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ

አብዛኛዎቹ አሽከርካሪዎች ቅጣቱ እንደደረሰባቸው ሳይውቁ ከአንድ ዓመት በኋላ ያልከፈሉት ቅጣት አለ የሚል የጽሁፍ መልዕክት ከነወለዱ እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል


በአዲስ
አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ከአደጋ ውጪ ያሉ ቅጣቶች ነጥብ እንዲሰረዝ ውሳኔ ቢያሳልፍም  ከቅጣት ገንዘብና ከወለድ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር አሁንም አላግባብ እንግልት እየፈጠረባቸው መሆኑን አሽከርካሪዎች ገለጹ።

አብዛኛዎቹ አሽከርካሪዎች ቅጣቱ እንደደረሰባቸው ሳይውቁ  ከአንድ ዓመት በኋላ ያልከፈሉት ቅጣት አለ የሚል የጽሁፍ መልዕክት  ከነወለዱ እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው አሽከርካሪ "መቀጣቴንም አላውቅም፣ ምንም የደረሰኝ የጽሁፍ መልዕክት የለም” ያለ ሲሆን የዛሬ ዓመት ያልከፈልከው ቅጣት አለ በሚል 23 ሺህ ብር ከነወለዱ እንዲከፈል መልዕክት እንደደረሰው አስረድቷል።

Advertisement
Your ad could be here — contact us

ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ደግሞ መንጃ ፈቃድ አውጥታ ነገር ግን ማሽከርከር ስላልቻለች ፈቃዱን እንደ መታወቂያ ብቻ እንደምትጠቀምበት ተናግራ፤ መንዳት ሳትጀምር የቅጣትና የወለድ ማስጠንቀቂያ እንደተላከላት አስረድታለች።


ቅሬታቸው በዚህ ብቻ አያበቃም ከመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ክፍያዎች ጋር የተያያዙ እንግልቶችም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል።


አሽከርካሪዎች ወደ ሆቴሎችና መናኸሪያዎች ፓርኪንግ ገብተው ሲወጡ በተፈጠረ የሲስተም ወይም የትኩረት ማነስ ሳቢያ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ የፓርኪንግ ክፍያው እስከ 288 ሺህ ብር ደርሶባቸው መገኘቱን ቅሬታ አቅራቢዎች ለሸገር ሬድዮ ተናግረዋል።

ተቋሙ ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ ደንብ ተላላፊ አሽከርካሪዎችን መንጃ ፈቃድ ከመንጠቅና ታርጋ ከመፍታት ወጥቶ ቅጣታቸውን በቴክኖሎጂ ሥርዓት ወደ ማስከፈል መሸጋገሩ ይታወሳል።



የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች እና አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር የወጣው አዲሱ ደንብ አሽከርካሪዎች የቅጣት ነጥባቸው 14 ከደረሰ መንጃ ፈቃዳቸው እንዲታገድ እና ጥፋት አጥፍተው 10 ቀን በላይ ሳይከፍሉ ከቆዩ በቀን 5 በመቶ ወለድ እንዲታከልበት ይደነግጋል።


ለተነሱት ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባ ተቆጣጣሪዎች ሲቀጡ የቅጣት ወረቀት አብረው እንዲሰጡ መደረጉን አስታውሰዋል።


መልዕክት ሳይደርሳቸው ለቆዩ አሽከርካሪዎችም ዳይሬክተሯ  በአቅራቢያ ወደሚገኙ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በመሄድ ወይም "Driver App" የተሰኘውን የሞባይል አፕሊኬሽን ከፕሌይ ስቶር ወይም አፕ ስቶር በማውረድ መረጃዎችን ማጣራት እንደሚቻል ጠቁመዋል።


በሲስተሙ በኩል ምንም አይነት ችግር እንደሌለ የሚናገሩት ዳይሬክተሯ ቴክስት አልደረሰንም የሚሉ አሽከርካሪዎች ወደ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በመሄድ ከየትኛው አካል ጋር ክፍተት እንደተፈጠረ በማረጋገጥ ማስተካከል እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢቲ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እስራኤል ብሩክ በበኩላቸው አዲስ ቴክኖሎጂ ሲተገበር ሊታገሱት የሚገቡ ክፍተቶች እንዳሉ አንስተዋል።


ሰው በባህሪው የአንድ ጊዜ ማሳሰቢያ ብቻ ተቀብሎ የሚዘነጋ በመሆኑ ሥርዓቱ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ የሚልክ የሶፍትዌር ማሻሻያ ሊኖረው እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።


የዲጂታል አሰራር ዋና ዓላማ የከተማን ትራፊክ አገልግሎት ማዘመን እንጂ የዜጎችን የመርሳት አጋጣሚ ቀጥታ ወደ ገቢ ምንጭነት መቀየር ሊሆን እንደማይገባ ያነሱት ባለሙያው ለአነስተኛ የፓርኪንግ እና የትራፊክ ጥፋቶች በየቀኑ ቅጣት ከማከማቸት ይልቅ አሽከርካሪዎች ዓመታዊ ቴክኒክ ምርመራ ሲያደርጉ ወይም ፈቃድ ሲያድሱ ክፍያውን በሚመጥን መልኩ እንዲከፍሉ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ይመክራሉ።

BS
ስለ ጸሐፊው

Bethelhem Solomon

80 ጽሁፎች
ሁሉንም ጽሁፎቻቸውን ይመልከቱ →

ተዛማጅ ጽሁፎች

አስተያየቶች (0)

አስተያየቶች ከመታተማቸው በፊት ይገመገማሉ።

አስተያየት በመስጠት የእኛን የአጠቃቀም ውሎች እና የግላዊነት ፖሊሲ ተቀብለዋል ማለት ነው።