የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፤ በየዓመቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ21 ሀገራት የሚገኙ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት ለጾታዊ ጥቃት ወይም ብዝበዛ መጋለጣቸውን አዲስ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
ዩኔሴፍ በሪፖርቱ በአፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን እንዲሁም ምሥራቅ አውሮፓ ባሉ ሀገራት የሚገኙ ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 17 ዓመት ከሆኑ አምስት ሕጻናት አንዱ ለዲጂታል መድረኮች ጥቃት ተጋላጭ ነው ብሏል፡፡
“Through Children's Eyes: How Digital Technologies Enable Child Sexual Abuse” በተሰኘው በዚህ ሪፖርት ላይ እንደተመላከተው 15 ሚሊዮን ገደማ ሕፃናት ያለፍላጎታቸው የጾታዊ ይዘት ያላቸውን ምሥሎችና ቪዲዮዎች እንዲመለከቱ ተደርገዋል።
9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናትም ያለፍላጎታቸው በጾታዊ ውይይቶች እንዲሳተፉ አልያም የጾታዊ ምሥሎቻቸውን እንዲልኩ መገደዳቸውን አመልክቷል፡፡ 4 ሚሊዮን ሕፃናት ደግሞ የግል ጾታዊ ምስሎቻቸው ያለ ፈቃዳቸው ለሌሎች ተሰራጭተውባቸዋል።
ከግማሽ በላይ የሚሆነው ጥቃት የተፈጸመው በዋና ዋና የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሲሆን ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት የተደረገው ከ1 በመቶ ያነሰው ብቻ እንደሆነ ሪፖርቱ አካቷል።
ይህም በቴክኖሎጂ አማካኝነት በኢንተርኔትም ሆነ ከአውታረ መረብ ውጭ የሚፈጸሙ የሕፃናት ጾታዊ ጥቃት እና ብዝበዛ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላክቷል።
ከጥቃቶቹ መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ዋትስአፕ፣ ስናፕቻት እና ቲክቶክ ባሉ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የተፈጸሙ ሲሆኑ 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በኢንተርኔት በሚጫወቱ ጨዋታዎች የተፈጸሙ ናቸው።
በሪፖርቱ የተካተተው ሌላው ግኝት ጥቃቱ የሚፈጸመው ከቅርብ ሰዎች በሚሰነዘር ጥቃትመሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ከተጠቂዎቹ መካከል 57 በመቶ የሚሆኑት ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ቀድመው በሚያውቋቸው ጓደኞቻቸው፣ የፍቅር አጋሮቻቸው ወይም የቤተሰብ አባላት ነው፡፡
ጥቃቱ በሕፃናት የሥነ ልቡና እና አእምሯዊ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ከመገኘቱም በላይ ሕይወታቸውን ለማጥፋት አልያም አካልን ለመጉዳት የመጋለጥ እድላቸው በ4 እጥፍ መጨመሩ ተረጋግጧል።
ሕጻናት በዲጂታል መድረኮች ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው የተናገሩት የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራሰል “ብዙዎቹ ወዴት እንደሚሄዱ ሳያውቁ በዝምታ ይሰቃያሉ፤ እኛ ደግሞ ይህንን ችግር እንዳላየን ልናልፈው አንችልም" ብለዋል።
ዩኒሴፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እና የማህበረሰብ አካላት አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወስዱ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መተግበሪያዎቻቸውን ሲቀርጹ የሕፃናትን ደህንነት እና የግል ሚስጥር በሚጠብቅ መልኩ እንዲሰሩ ማድረግ አለባቸው ሲል አሳስቧል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአሜሪካው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሜታ ታዳጊዎችን ለአደጋ እና ለማህበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት የሚያጋልጡ አሰራሮችን ተጠቅሟል በሚል በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወቃል። እንዲሁም የተለያዩ የዓለም ሀገራት የታዳጊዎች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን እና ዝቅተኛ እድሜን የሚገድቡ ህጎች በማርቀቅ ላይ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ 20 ሚሊዮን ገደማ ሕፃናት በኢንተርኔት አማካኝነት ለጾታዊ ጥቃት ተጋልጠዋል - ዩኒሴፍ
አጋራ፦
ይህም በቴክኖሎጂ አማካኝነት በኢንተርኔትም ሆነ ከአውታረ መረብ ውጭ የሚፈጸሙ የሕፃናት ጾታዊ ጥቃት እና ብዝበዛ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላክቷል።
← Previous
የአሽከርካሪዎችን የጡረታና የሥራ ውል መብት የሚያስከብር ስምምነት ተደረገ
Next →
የአፍሪካን እውነተኛ ግዙፍነት የሚያሳይ አዲስ ካርታ ጸደቀ